የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለ32ኛ ዙር ያስተማራቸውን 1 ሺህ 387 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት አስመርቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፣ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባሳዩት ዓላማ ጽናትና ዕውቀት ለአዲስ ምዕራፍ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ዓለም በፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋትና በአካባቢ ጥበቃ ተግዳሮቶች ምክንያት ከፍተኛ የለውጥ ግፊት ውስጥ እንደምትገኝ ጠቁመው፣ ሀገራት ዘላቂ ልማትንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማረጋገጥ ለዕውቀትና ለፈጠራ ትኩረት መስጠት አማራጭ የሌለው ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተ.መ.ድ. ዘላቂ የልማት ግቦችንና የአፍሪካ ሕብረትን የ2063 አጀንዳ ራዕይ ለማሳካት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሣሪያዎች መሆናቸውን ያብራሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋን የምታፋጥነበትን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ራዕይ ቀርጻ ወደ ተግባር መግባቷን ገልጸዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ)፣ የመረጃ ሳይንስ፣ ሮቦቲክስና ባዮቴክኖሎጂ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አዳዲስ አድማሶችን እየከፈቱ በመሆኑ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገራችን ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ ምርምር የማካሄድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርና የዓለምን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ ባለራዕይ ተመራማሪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ጭምር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ተመራቂዎች ራሳቸውን ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች አድርገው እንዲመለከቱና የመማራቸው እውነተኛ ዋጋ በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ በሚያመጡት አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚለካ በመገንዘብ፣ በቀጣይ በሚሰማሩበት የሥራና የሕይወት መስክ ሁሉ ስኬትና መልካም እድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።
ተመራቂዎቹ በተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮች በመጀመርያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በሶስተኛ ዲግሪ ወይም በዶክትሬት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።
