ሐምሌ ወር ላይ እንገኛለን፤ የክረምቱ ዝናብ ምድርን በእርጥበት ሲያለመልም፣ የኢትዮጵያ ለምነት በአረንጓዴ ቀለም የሚታይበት ወቅት ይጀምራል።
ይህ ወር ለገበሬው የዘር ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ሕዝብ ችግኝ በመትከል ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ተስፋን የሚያስቀምጥበት ወቅት ነው።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች በጉምና በጭጋግ ይሸፈናሉ። ለገበሬው ግን ይህ የዕረፍት ጊዜ ሳይሆን የብርቱ ሥራ ወቅት ነው። ከማለዳ ጀምሮ ማረሻውን ይዞ ወደ ማሳው ያመራል፤ በክረምቱ ዝናብ የረሰረሰችው መሬትም ዘርን ለመቀበል ዝግጁ ትሆናለች።
የኢትዮጵያ ክረምት ወር ግን በማረስና በመዝራት ብቻ አይገለጽም። የተራቆቱ ተራሮችን እንደገና አረንጓዴ መልበስ፣ የአፈርና የውኃ ሀብትን መጠበቅ፣ የወደፊቱን የአየር ንብረት መጠናከርም የዚህ ወቅት አካል ሆኗል። በዚህ ላይ ነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልቅ ፋይዳውን የሚያሳየው።
ገበሬው ማሳውን ሲያርስ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ችግኝ በመትከል ለም አፈሩ በዝናብ እንዳይታጠብ ይከላከላሉ፤ የተራቆተው መሬትም ዳግም አረንጓዴ መልክ ይላበሳል።
ከዓመት እስከ ዓመት የተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ ነው። በከተሞች የተፈጠሩ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ በየክልሉ እየለሙ ያሉ ደኖች እና የተሻሻሉ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳሮች የተከታታይ ጥረቱ ማሳያዎች ሆነዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት ግን በአንድ ቀን ችግኝ በመትከል ብቻ አይለካም። በበጋው የተዘጋጁ ጉድጓዶች በሐምሌ ችግኞችን ይቀበላሉ፤ ክረምት ካለፈ በኋላ ደግሞ በመኮትኮት፣ በማጠጣትና በመንከባከብ እንዲያድጉ ይደረጋል። የንቅናቄው ጥንካሬም ከተከላው በላይ በእንክብካቤው ውስጥ ይገኛል።
በዚህም ዝናቡ መሬትን ያለመልማል፤ የኢትዮጵያውያን እጆች ደግሞ ችግኝ ይተክላሉ። ይህ የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር የሀገር ግንባታ ባህል ሆኗል።
በዚህ ዘመቻ ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ከዓለም አቀፍ ሪከርድ እስከ መስበር እና ሽልማቶችን በማግኘት ታሪክ ፅፏል።
የሀገራችን የደን ሽፋን ከነበረበት 17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማደግ ችሏል።
ለዚህ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ሙሉ በሙሉ ደርቆ የነበረው የሀሮማያ ሐይቅ በአረንጓዴ ዐሻራ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ምክንያት ዳግም ህያው መሆን መቻሉ ነው።
እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ ባለብዙ ጥቅም ችግኞች በመተከላቸው፣ ኢትዮጵያ በውጭ በመላክ ተጠቃሚ ሀገር ለመሆን በቅታለች።
በዚህም አላበቃም በተለይ በከፍተኛ የሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የሌሎች ሀገራት ሚኒስትሮችና አመራሮች የአረንጓዴ ዐሻራቸውን በማኖር ትልቅ ምሳሌ ሆነዋል።
የሐምሌ ዝናብ ዛሬን ሲያለመልም፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ደግሞ ነገን ያሳድጋል፤ ከዓመት እስከ ዓመት የሚቀጥለው ይህ ጉዞም ለኢትዮጵያ ዘላቂ አረንጓዴ የወደፊት ተስፋን የሚያስተሳስር ድልድይ ነው።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: