ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው ሁለንተናዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የዲጂታል አገልግሎት መስፋፋት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ምቹ ምህዳር መፍጠራቸውን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
መንግሥት ለንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ተከትሎ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ እስራኤልና ኢትዮጵያ የጠበቀ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ቡና እና ሰሊጥን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ከኢትዮጵያ ያስገባሉ።
የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ለኢትዮጵያ እያካፈሉ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የዲጂታላይዜሽን ግስጋሴው እስራኤል በኢትዮጵያ ያላትን ኢንቨስትመንት ይበልጥ እንድታስፋፋ ምቹ መደላድል ፈጥሯል ብለዋል።
በተመሳሳይ የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ፓራናቪታና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምታደርገውን ጥረትና የምታቀርባቸውን ማበረታቻዎች አድንቀዋል።
ስሪላንካ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ላይ በስፋት እየተሳተፈች የምትገኝ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች አማራጭ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ሙሉ ፍላጎት እንዳላት ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ተወካይ ባሲት ሳሊም ሻህ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለንግድ እጅግ ምቹ የሆነ ስትራቴጂካዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት ጠቅሰው፤ እንደ ቡና እና ጥራጥሬ ያሉ ምርቶችን ወደ ሀገራቸው እያስገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓኪስታን በቀጣይም የንግድ ግንኙነቱን ከማሳደግ ባለፈ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎችም ጭምር ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: