ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ዘንድሮ ከ10.2 እስከ 10.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ አስደናቂ አሃዝ በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት ነው።
ይህ የኢትዮጵያ ዕድገት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር ብቻ ሳይሆን በመልክ፣ በባህሪ እና በይዘቱ ፈጽሞ የተለየና ጥልቅ መዋቅራዊ ሽግግርን ያረጋገጠ ነው።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ብድር (Commercial loan) ወስደው የሰራተኛ ደመወዝ በሚከፍሉበት እና በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ግን ላለፉት 8 ዓመታት አንድም ዶላር የንግድ ብድር አልወሰደችም።
ይልቁንም፣ የመደመር መንግስትን "የትብብር ሞዴል" በመከተልና የዕዳ ሽግሽግ በማድረግ የብድር መጠኗን ከ50 በመቶ በታች በማውረድ ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ገንብታለች። ይህ ስትራቴጂካዊ የፋይናንስ አስተዳደር ኢትዮጵያን ከአህጉሪቱ ሀገራት በእጅጉ የተለየችና ሉዓላዊነቷን በኢኮኖሚ ያረጋገጠች ያደርጋታል።
የኢትዮጵያ ዕድገት ሌላው ልዩ ባህሪ በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አለመሆኑ ነው። አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን ሀገራት በጥሬ እቃ ኤክስፖርት ላይ ብቻ ሲደገፉ፣ የኢትዮጵያ ዕድገት ግን ሁለንተናዊና ብዝኃ ዘርፍ (Diversified) ነው።
በግብርናው ዘርፍ በክላስተር ማረስን በማስፋፋት 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 1.3 ቢሊየን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ዘርፉ የ7.7 በመቶ ዕድገት ያሳያል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ ነባር ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን ከ47 ወደ 67 በመቶ ያሳደጉ ሲሆን፣ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የውጭ ምርቶችን (እንደ ሲሚንቶ፣ ብረትና መስታወት ያሉትን) በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት በመቻሉ ዘርፉ የ12.7 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል። የአገልግሎት ዘርፉ በ9.8 በመቶ ሲያድግ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚው ደግሞ በ5 ሚሊየን ኮደርስ ፕሮጀክት ታግዞ ትልቅ ዝላይ እያሳየ ነው።
ከሁሉም በላይ ይህ ሁለንተናዊ ዕድገት ቁጥራዊ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረገ በተግባር የሚዳሰስ ውጤት ነው። በአንድ አመት ብቻ በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ስምሪት እና በርቀት ስራ በአጠቃላይ ከ5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል።
የዜጎችን የኑሮ ጫና (Cost of Living) ለማቃለል መንግስት በየወሩ 36 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ድጎማ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከ2,000 በላይ የእሁድ ገበያዎችን አቋቁሟል። መሰረታዊ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታትም በሚቀጥሉት 5 ዓመታት 1.5 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
የጤናውን ዘርፍ ስንመለከትም፣ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ማምረት አቅም ከ4 በመቶ ወደ 44-45 በመቶ ከፍ በማለቱ ዜጎች የተሻለ የህክምና አቅርቦት እያገኙ ነው።
ይህ ሁለገብ ዕድገት ከተማን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም ያካተተ ነው። የገጠር ነዋሪው የገጠር ኮሪደር፣ የዘመናዊ ግብርና፣ የሶላር፣ የባዮጋዝና የዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ መሆን መጀመሩ ዕድገቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያዳረሰ (Inclusive) መሆኑን ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዕድገት የመደመር መንግስት በሚያራምደው የፍጥነት፣ የፈጠራ እና የትብብር መርህ የሚመራ በመሆኑ፣ ሀገሪቱ ያላትን ዕምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የህዝብ ብልጽግና እየቀየረች ትገኛለች። ይህ ሚዛኑን የጠበቀ፣ የዜጎችን ኑሮ ያሻሻለና ጫናዎችን የሚቋቋም የዕድገት ሞዴል ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ ከማድረግ አልፎ፣ ለመላው አፍሪካም ትልቅ ተምሳሌት የሚያደርጋት ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: