Search

ሀገራዊ ምክክር የትውልድ ዕዳ መክፈያ ወርቃማ ዕድል

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 63

ኢትዮጵያ ረጅምና ውስብስብ የፖለቲካ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ዳሩ ግን ይህ የታሪክ ጉዞ ሁልጊዜም በሰላማዊ ውይይት እና በሐሳብ የበላይነት የተቃኘ አልነበረም።

ለዘመናት የሀገራችን ዋነኛ የፖለቲካ ልዩነት መፍቻ መንገዶች የጠብመንጃ አፈሙዝ፣ የጦርነት አውድማ እና አንዱ ሌላውን የማሸነፍ ግብግብ ነበሩ።

ሀገራችን ጦርነትን በተደጋጋሚ ሞክራዋለች፤ ምክክርን ግን ተቋማዊ አድርጋ ሞክራው አታውቅም።

አሁን በዋዜማ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ይህንን ለዘመናት የዘለቀ አውዳሚ ባህል ለመቀየር ፍፁም ወርቃማ የታሪክ ዕድል ነው።

በተለይም ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በማካተት የፊታችን ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2018 .. የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ ሀገራችን ወደ አዲስ የሰላም እና የዴሞክራሲ ምዕራፍ የመሻገር ደጃፍ ላይ የምትገኝበት ታሪካዊ ወቅት ነው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ልዩነቶችን በሐሳብ ስምምነት መፍታት ባለመቻሉ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ተከፍሏል። በዚህም ትውልዶች አልቀዋል፤ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ማኅበራዊ ትስስሮችም ላልተዋል።

ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ከልዩነቶች በላይ የሚያስማማ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበት የታሪክ ምዕራፍ ተፈጥሮ እና ተሞክሮ ስለማያውቅ ነው።

የአሁኑ ሀገራዊ ምክክር ከወቅታዊ የፖለቲካ ክስተት በላይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባውም ለዚህ ነው።

ይህ ሂደት ኢትዮጵያውያን "ከእርስ በእርስ መጋጨት ወደ ሐሳብ የበላይነት" የተሻገሩበት፣ ጠብመንጃን አስቀምጠው ስለ ሀገራቸው የወደፊት እጣ ፈንታ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገር የወሰኑበት የመጀመሪያው የታሪክ ምዕራፍ ነው።

የዚህ ምክክር ትልቁ ስኬት ከውጤቱ ይልቅ ሂደቱ ራሱ ነው። በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድ ጣሪያ ስር ተሰብስበው እንዲወያዩ መደረጉ በራሱ ትልቅ ድል ነው።

ችግሮችን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል ተብሎ ጉባኤው መመቻቸቱ አዲስ የመግባባት ዴሞክራሲ ባህል መግቢያ ነው።

ይህ አዲስ ታሪክ በጠብመንጃ ኃይል ፍላጎትን የመጫን አባዜ በተስፋ መቁረጥ እንዲደመደም የሚያደርግ ብሩህ የተስፋ ማብሰሪያ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተሸከመችው የበቀል እና የጥላቻ ሰንሰለት ተላቅቃ አዲስ እና ሉዓላዊ የሐሳብ የበላይነት ማማ ላይ የምትወጣበት የእርቅ መሠረት ነው።

እያንዳንዱ ዜጋ ልዩነቱን የውበት እና የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ በመቀበል የነገዋን የበለጸገች እና የተረጋጋች ሀገር በትብብር ለመገንባት ቃሉን የሚያድስበት ብቸኛ እና ታሪካዊ መድረክም ነው።

ለዘመናት የሞከርነው ጦርነት አብቅቶ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክክርን በይፋ ለመጀመር በዋዜማው ላይ እንገኛለን።

ይህንን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እና ሂደቱን ማገዝ የሁሉም ዜጋ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የኢትዮጵያ አዲስ መለያ፣ የመጻኢው ትውልድ ደግሞ የሰላም እና የዴሞክራሲ ባለቤት መሆኛ መተማመኛ ዋስትና ነው።

ይህ የጋራ ድል የኢትዮጵያን ትንሣኤ በተግባር የሚያረጋግጥ እና የትውልድ ዕዳን የሚከፍል ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: