Search

ኢትዮጵያ ወደ ታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 44

የዘመናት ቅሬታዎችን ለመፍታት፣ በጋራ እሴቶች ላይ ለመስማማት እና ለነገዋ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መሠረት ለመጣል የሀገራዊ ምክክር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

የሐምሌ 8 የምክክር ጉባኤ ሀገራችን ታሪካዊ ለውጥ ሊታይ የምትችልበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየቀበሌው እና በየዞኑ ሲወያዩባቸው የቆዩአቸው አጀንዳዎች ተጠቃልለው የመጨረሻ ውሳኔና አቅጣጫ የሚቀመጥበት ታሪካዊ መገናኛ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታት በመላው ሀገራችን የተሰበሰቡ አጀንዳዎች፣ የተመረጡ ተወካዮች እና የተደራጁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ ተለይተው በዚህ ሳምንት በዋናው ጉባኤ ላይ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ይቀርባሉ።

ላለፉት ቀናት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እና ባለድርሻ አካላት ለዚሁ መድረክ አስፈላጊ የሆኑ የደኅንነት እና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶች በበቂ ሁኔታ እየተደረጉ ቆይተዋል።

ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጡ 4 ሺህ ተመካካሪዎች ዋናው ጉባኤ ወደ ሚካሄድበት ማዕከል አዲስ አበባ ገብተዋል።

ይህ ዋና ጉባኤ ካለፉት የምክክር ሂደቶች በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይለያል። እስካሁን የተነሱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ስብራት ጥያቄዎች ተለይተው፣ የጋራ መፍትሔ ምክረ-ሐሳብ የሚቀረጽበት መድረክ እንዲሁም ከጉባኤው የሚወጡት ውጤቶች ለሀገራችን የፖለቲካ እና የሕግ ማሻሻያዎች እንደ ፍኖተ-ካርታ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው።

ይህ ምክክር በለፉት ትውልዶች የተገነቡ የልዩነት ግንብ አፍርሰን ለሚቀጥለው ትውልድ የምንሻገርበት ድልድይ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ንቁ ተሳትፎና ክፍት ልብ ወሳኝ ነው።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: