የሀገራችን ኩራትና ልዩ መለያ የሆነው ጤፍ ዛሬ ላይ ድንበር ተሻግሮ የዓለምን ማዕድ እያደመቀ ይገኛል።
ለዚህም በጤፍ አምራችነቱ በሚታወቀው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ ተወልዶ ያደገው የ32 ዓመት ወጣት ሰማኸኝ ጌታቸው የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ያደረገ “ማኛ ጤፍ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እና ኤክስፖርት” ድርጅትን ከአንድ ዓመት በፊት አቋቁሞ ወደ ሥራ አስገብቷል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ በመሆን በከፈተው ድርጅት በየዕለቱ ከ600 እስከ 800 ኩንታል ጤፍ በማቀነባበርና ፈጭቶ ደረጃውን በጠበቀ መልክ ለዓለም ገበያ እያቀረበ ይገኛል።
በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ600 ቶን በላይ የተፈጨ ማኛ ጤፍን ለአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ስዊዘርላንድ ገበያ በመላክ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሀገር አስገኝቷል።
ምርቱ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ዜጎችንም ቀልብ መግዛት መቻሉን የሚገልጸው ወጣት ሰማኸኝ፣ ፍላጎቱና ተቀባይነቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡
በሥራው ለ40 ቋሚ እና ለ30 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና በቀጣይም የጤፍ ፓስታ እና መኮረኒ ፋብሪካን በመክፈት የጤፍን እሴት ይበልጥ አሳድጎ በዓለም ገበያ ለማቅረብ ማቀዱን ገልጿል።
ለስኬቱ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ላደረገለት ድጋፍ ምስጋና ያቀረበው ወጣት ሰማኸኝ፣ ሥራውን ይበልጥ ለማስፋፋትና የኤክስፖርት ገቢን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርግ ጠይቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያም፣ ለዚህ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥ አዲስና ይበልጥ የተሻለ ዕድልን ይዞ የመጣ በመሆኑ ይህንን እውን ማድረግ ለቻሉ ሁሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: