Search

የራሳችን አጀንዳ በራሳችን ጠረጴዛ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 39

ምክክር ዝም ብሎ የፖለቲካ ልምምድ ሳይሆን፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕልውና ፅኑ መሠረት ነው።

በታሪክ እንደምናየው፣ ጠንካራ እና የማይበገሩ ሀገራት የተፈጠሩት፣ እንዲሁም የተግባባ እና አንድነቱ የፀና ሕዝብ የታነፀው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ የሠለጠነ የውይይት ባህል ነው።

ዜጎች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው አንደበት ሲወስኑ፣ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ እና በሰከነ መንገድ ሲያርቁ፣ ሀገራዊ አንድነት በማይናወጥ አለት ላይ ይቆማል።

"የራሳችን አጀንዳ በራሳችን ጠረጴዛ" የሚለው ታላቅ እሳቤ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በፅኑ በመዝጋት የሀገርን የውስጥ ችግር በቤተሰብ መማከር የመፍታት የብሔራዊ ጥቅም እና የሉዓላዊነት ልዕል አጀንዳ ነው።

በአንጻሩ፣ ያልተመካከረ እና የማይደማመጥ ማኅበረሰብ ሁልጊዜም ለውድቀት እና ለክፋት የተጋለጠ ነው።

ኢትዮጵያችን ባለፉት ዘመናት መራራ ዋጋ የከፈለችው፣ የፖለቲካ ስብራቶች ሲያደሟት የኖሩት በዚህ የውይይት እና የመደማመጥ ድርቅ ምክንያት ነው።

መመካከር እና መነጋገር ሲያቅተን፣ አንዱ የገዛ ወንድሙን በጠላትነት ሲፈርጅ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ የጥፋት ጦር ሲያነሳ፣ ሀገራችን ለእርስ በርስ የሲቪል ጦርነት እና ለውጭ ጠላት አፍራሽ ሴራ ተጋልጣ ኖራለች።

ያልተመካከረ ሕዝብ የተከፋፈለ ማኅበረሰብን፣ የደከመ ሀገረ-መንግሥትን እና በቀላሉ የሚደፈርን ደካማ ድንበር ይፈጥራል።

ችግሮቻችንን በራሳችን አቅም ከመፍታት ይልቅ፣ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ እስከመሆን ያደረሰን ይኸው መነጋገርን የመፀየፍ የታሪክ አባዜ ነበር።

ዛሬ ግን፣ ከጨለማው ታሪካችን ስህተት ተምረን፣ የራሳችንን አጀንዳ አቅፈን፣ በገዛ ጠረጴዛችን ዙሪያ ለመቀመጥ ታሪካዊ ውሳኔ ላይ ደርሰናል። የራሳችንን ውስብስብ ችግር በራሳችን ጥበብ፣ ባህል እና ሀገር በቀል ምክክር ስንፈታ፣ ሉዓላዊነታችንን በተግባር እናረጋግጣለን።

ሀገራዊ ምክክር ሀገርን ከውድቀት አፋፍ ታድጎ፣ ጠንካራ ማኅበራዊ ውልን የምንገነባበት የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው።

ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ "እኛ" በሚል የጋራ መንፈስ ስንመክር፣ የውጭ ጠላት ያፍራል፤ የተበታተነው ኃይላችን ወደ አንድ ይሰበሰባል፤ ደካማው ሀገረ-መንግሥታችን ጠንክሮ ይወጣል።

አዎ! የራሳችን አጀንዳ በራሳችን ጠረጴዛ ላይ ሲመከር፣ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ክብሯ፣ በአንድነቷ እና በልጆቿ የውይይት ጥበብ ለዘላለም አሸናፊ ሆና ትዘልቃለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: