የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ አስተዳር ምክር ቤት ባካሄደው 3ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ በሁለተኛ ቀን ውሎው በከተማዋ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በመወያየት፣ የአስተዳደሩን አጠቃላይ በጀት 502 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር እንዲሆን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡
የፀደቀው በጀት ከባለፈው የ2018 ዓ.ም ተመሳሳይ በጀት ጋር ሲነጻፀር የ152 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ወይም 43 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ከፀደቀው በጀት ውስጥ 359 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለካፒታል፣ 142 ነጥብ 97 ቢሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ እንዲሁም 16 ቢሊየን ብር የመጠባበቂያ በጀት መሆኑ ተመላክቷል።
በጀቱ የከተማ አስተዳደሩን የ10 እና የ5 ዓመት የልማት ስትራቴጂዎች ግቦችንና እና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማሳካት ያለመ ነው መባሉን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
የኢኮኖሚ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ የሥራ እድል፣ ፈጠራ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማጠናከር፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና ጥገና በዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ኮሪደር ልማትን ጨምሮ መጠበቅና ለማስቀጠል የሚውል እንደሆነም ተገልጿል።
እንዲሁም የትራንስፖርትና የትራፊክ ፍሰትን ማሻሻል፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሹ አሠራርንና ሌብነትን ማስቀረት፣ የሰው ሃብት ልማት የማስፈፀም አቅምን መገንባት፣ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ፣ የቤት ልማት ማጠናከር የውሃ አቅርቦት እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በተሟላ ለማጠናቀቅ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት የሚውል መሆኑ በቀረበው የበጀት ማብራሪያ ተመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: