የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ የተረጋጋ መሆኑን እንዲሁም የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገት መረጋጋት ማሳየቱን የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ በሀገራችን ያለው የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የወለድ በተመለከተ የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን እና ከማስቀመጫ ወለድ ውጭ ያሉት በሙሉ ከዜሮ በላይ መሆናቸውን መግለጫው አትቷል፡፡
በግንቦት ወር 2018 የሁሉም የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶች አማካይ የወለድ ምጣኔ እና የ91 ቀን የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ አማካይ የወለድ ምጣኔ በቅደም ተከተል 12.3 እና 11 በመቶ በመሆን ካለፈው ዓመት ቅናሽ አሳይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ በተለይ በአጭር ጊዜ ሰነዶች ላይ ወደ 667.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ከፍተኛ የተጨማሪ ፍላጎት ተመዝግቧል፡፡
የኢንቨስትመንት ባንኮች ተሳትፎ መጨመር ገበያውን ይበልጥ እንዳሰፋው ነው ኮሚቴው በመግለጫው የጠቀሰው፡፡
ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ አማካይ የወለድ ምጣኔ በመጋቢት ወር 2018 ከነበረው 18.0 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በግንቦት ወር 2018 ወደ 14.6 በመቶ ደርሷል፡፡
በዚህም የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ አጠቃላይ የግብይት መጠንም 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ የባንክና የፋይናንስ ዘርፉ በቂ ካፒታል ያለው እና የተበላሸ ብድር መጠኑ ዝቅተኛ በመሆኑ ጤናማ እና የተረጋጋ ሆኖ መቀጠሉን ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡
ለዚህ አዎንታዊ አፈፃፀም የአጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት ማደግ እና የብድር ተመላሽ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
የባንኮችን ጤናማነት በይበልጥ ከሚያሳዩት አንዱ የሆነው የግል ባንኮች የብድር እና የተቀማጭ ሂሳብ ምጣኔ በ2016 ከነበረው 90.3 በመቶ በ2018 ወደ 72.7 በመቶ ዝቅ ማለቱ፣ የባንኮች የገንዘብ አስተዳደር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን እንደሚያሳይ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: