Search

ወርቃማው አማካይ - አዲሱ መንገድ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 63

የሰው ልጅ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ ልዩነቶች የውበት እና የጥንካሬ ምንጭ መሆን የሚችሉት በውይይት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ መስተጋብር ሲኖር ብቻ ነው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ የሚያስማማን ስፍራ ማግኘት የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

ወርቃማው አማካይ ማለት አንዱ ሌላውን ውጦ የሚያጠፋበት ወይም የራሱን እሳቤ ብቻ በግድ የሚጭንበት ሳይሆን፣ ሁሉም የየራሱን ቀለም ይዞ በአንድ ውብ ሸራ ላይ የሚያርፍበት ማኅበራዊ ስምምነት ነው።

ምክክር ለሁሉም ተስማሚ የሆነውን ወርቃማ አማካይ ያዋልዳል። ይህ ወርቃማ አማካይ ማንም የማይገፋበት፣ ሁሉንም አቅፎ የሚይዝ የጋራ መጓዣ መንገድ ነው።

ባለፉት ዘመናት ነጠላ መንገዶች የት እንዳደረሱን በገዛ ታሪካችን አይተናል። አንድን አመለካከት ብቻ ፍጹም እውነት አድርጎ በመውሰድ ሌላውን ማግለል ዋጋ አስከፍሎናል።

ነጠላ እሳቤ እንደ ኢትዮጵያ፣ ብዝኃ ፍላጎትና ሰፊ ብዝኃነት ባለበት ሀገር የጥፋትና የመለያየት መንገድ መሆኑን በግልፅ ተገንዝበናል። የእኔ መንገድ ብቻ ትክክል ነው የሚል ግትርነት እርስ በርስ እንድንጠራጠር፣ እንድንጋጭና እንድንደማማ አድርጎናል።

የሕዝቦችን የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ባህሎችና ታሪካዊ ዳራዎች በአንድ ጠባብ ቱቦ ውስጥ ለማሳለፍ መሞከር ውጥረትን እንጂ ሰላምን አላመጣም። እያንዳንዱ ቡድን የራሱን ፅንፍ ይዞ ሲጓዝ፣ ሀገር የምትባለው የጋራ መኖሪያችን መሠረት ይናጋል። ስለዚህ ከተጓዝንበት የጥፋት መንገድ ተመልሰን፣ ወደ መሃል መምጣት አለብን።

ወርቃማው አማካይ ፅንፎች የሚለዝቡበት፣ እልህ በምክንያት የሚተካበት የብስለት መድረክ ነው። እዚህ ስፍራ ላይ ለመድረስ እውነተኛና ሁሉን አቀፍ ምክክር እጅግ ወሳኝ ነው።

ምክክር ሲባል አንዱ ሌላውን በንግግር አሸንፎ ለማንበርከክ የሚሞክርበት የጦር ሜዳ ሳይሆን፣ የጋራ ህመማችንን ተረድተን የጋራ መፍትሄ የምንሻበት የፈውስ ሂደት ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ መደማመጥ ከመነጋገር እኩል፣ አልፎ ተርፎም የበለጠ ዋጋ ይሰጠዋል። የሌላውን ስጋት እንደራስ ስጋት ማየት፣ የሌላውን ጥያቄ በፍትሃዊነት መመዘን ወደ ወርቃማው አማካይ ለምናደርገው ጉዞ ስንቅ ይሆነናል።

ብዝኃነት ባለባት ሀገራችን፣ የሁሉንም ፍላጎት መቶ በመቶ ማሟላት ባይቻልም፣ ማንም ፍፁም ተሸናፊ የማይሆንበትን የጋራ ስምምነት መፍጠር ግን ይቻላል።

ብዝኃነታችን የጥፋት ሳይሆን የልማት፣ የመለያየት ሳይሆን የአንድነት መሠረት እንዲሆን ካስፈለገ፣ የሚያስማማን ስፍራ ላይ መገናኘት ግድ ይለናል። በውይይትና በመግባባት የምንደርስበት ወርቃማ አማካይ ለልጆቻችን ሰላማዊና የበለፀገች ሀገር ለማስረከብ ብቸኛው አማራጭ ነው።

ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው፣ ማንም እንደማይገፋ በተግባር በማረጋገጥ፣ በእውነተኛ ምክክር ላይ የተመሠረተች ጠንካራ ሀገር እንገንባ። ይህም ለሁሉም የምትበቃን አንዲት ሉዓላዊት ኢትዮጵያን እውን ያደርጋል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: