Search

የኢትዮጵያ እና የቤኒን አጋርነት - ከአቪዬሽን እስከ ተፈጥሮ ጥበቃ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 57

የቤኒን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገኛሉ።

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ዋዳግኒ .. ሜይ 24 ቀን 2026 በይፋ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የዛሬው የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከመጀመሪያዎቹ የውጭ ሀገር ጉብኝቶቻቸው አንዱ ነው።

ጉብኝቱ ሀገራቸው ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ለማጠናከር ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይና ትልቅ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው ነው።

በዚሁ አግባብ፣ ፕሬዚዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ጋር በሁለትዮሽ እና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ተፈጥሯዊ መመሳሰል እና የጋራ ዕድሎች

የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ባለፈ በተፈጥሮ ሀብት እና የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ሰፊ የጋራ መድረክ አለው።

ቤኒን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ እንደ ፔንድጃሪ እና W ብሔራዊ ፓርኮችን የመሰሉ፣ ለምዕራብ አፍሪካ አንበሶች እና ዝሆኖች መጠለያ የሆኑ ታላላቅ የሥነ-ምህዳር ሀብቶች ባለቤት ናት።

ምንም እንኳን በሳህል ቀጣና ያለው የፀጥታ ስጋት ለፓርኮቹ ተግዳሮት ቢሆንም፣ መንግሥት ጥበቃውን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ይህ የቤኒን የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የቱሪዝም ልማት ራዕይ ጋር በእጅጉ የተጣጣመ ነው።

በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት ሀገራቱ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ውስጥ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ፣ እንዲሁም በግብርና ቴክኖሎጂ እና በቱሪዝም ልማት በጋራ ለመሥራት ሰፊ ዕድል ከፍቶላቸዋል።

ጠንካራ ታሪካዊ መሠረት እና የአቪዬሽን ትስስር

በኢትዮጵያ እና በቤኒን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቤኒን 2005 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከከፈተች በኋላ እያደገ መጥቷል።

በተለይም 2013 በአዲስ አበባ የተፈረመው አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለግብርና፣ ትምህርት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሕጋዊ መሠረት ጥሏል።

ይህን ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በመቀየር ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው።

አየር መንገዱ ወደ ቤኒን የኢኮኖሚ መዲና ኮቶኑ የሚያደርገውን ቀጥተኛ በረራ ማስፋቱ፣ እንዲሁም ቤኒን የአየር ትራንስፖርት ዘርፏን ክፍት ማድረጓ የአህጉራዊ ትስስር ራዕይ ያነገበችውን ኢትዮጵያን ከምዕራብ አፍሪካ ጋር ይበልጥ ያዋህዳታል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: