Search

ሀገራዊ ምክክር እና የፖለቲካ ባህል ለውጥ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 62

ኢትዮጵያ ድህነት እና ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስብራቶች ለዘመናት ስትፈተን ኖራለች።

እነዚህን የቆዩ ቅራኔዎች ለመፍታት እና በጠመንጃ አፈሙዝ ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ባህል ወደ ውይይት ለመቀየር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመፍትሔ ቁልፍ ሆኖ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (/) እንደሚሉት፥ ምክክር ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም። በየማኅበረሰቡ ባህል እና ሃይማኖት ውስጥ ያለው የዕርቅ እሴት፣ በዘመናዊ ኮሚሽን መልክ ወደ ሀገራዊ ደረጃ መምጣቱ፣ የተሟላ ሰላምን ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪል ማኅበራት እና የታጠቁ ቡድኖች አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ሥራ መሥራቱን ጠቅሰዋል።

ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አካላትን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃሳብና አጀንዳ የተካተተበት ሂደት መሆኑንም ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ትልቁ ስኬት የጦርነት ወሬ ቀርቶ ሰዎች ተወያይተው ለሀገራቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ መምከራቸው እንደሆነ ያስረዳሉ ኮሚሽነር ዮናስ።

ኢትዮጵያ እስካሁን የገጠማት ትልቁ ተግዳሮት በሃሳብ መለያየትን እንደ አማራጭ ከመውሰድ ይልቅ ኃይል መጠቀምን እና ግጭትን የፖለቲካ ትግል መገለጫ ማድረጓ እንደሆነ ምሁራን ይገልጻሉ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፥ የሀገረ መንግሥታችን ፖለቲካ ለብዙ ዓመታት በጠመንጃ አፈሙዝ ላይ የተመሠረተ እንደነበር ያነሳሉ።

የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ውረድ እንውረድ የታጀበ እና ግጭት የሞላበት እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን ይህን ልምምድ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም ወደሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመቀየር እየተሞከረ ነው ብለዋል።

የስምረት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እንደሚሉት፥ በሀገራችን ሰላም እና ዴሞክራሲ ይረጋገጥ ዘንድ ወደ መሀል መምጣት የግድ አስፈላጊ ነው።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ (/) ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ አቋም ላይ መግባባት አለብን፤ በጦርነት ማንበርከክ እንደ አማራጭ መወሰድ የለበትም ይላሉ።

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው፥ "ሕዝቡ መብቱን ያውቃል፤ አጀንዳችንን አስቀምጠን በመፎካከር፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት፤ ሕዝባችንን አዋህደን ወደፊት መጓዝ እንችላለን" በማለት ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቱኒዚያ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮዎች በመቀመር በብሔራዊ መግባባት የሕዝባችንን አንድነት የማጠናከር ግብ ሰንቋል።

ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ በሕዝብና በመንግሥት እንዲሁም በሕዝብና ሕዝብ መካከል መተማመንን ለመገንባት እና ለሁሉም የፖለቲካ ችግሮች መፍቻ ምክክርን ባህል ለማድረግ ያለመ ነው።

ከምክክሩ ከሚጠበቁ ውጤቶች አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ቀድሞው የጠብመንጃ ድምፅ መስማት ሳይሆን የውይይት እና የሰላም ተስፋን መመልከቱ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያምናል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: