Search

የመንግሥት የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ወደ 0.9 በመቶ ዝቅ ብሏል - የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 68

በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የበጀት ፖሊሲ ሥርዓት ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት እና ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው አስታውቋል።

በተለይም 2016 በጀት ዓመት ከተተገበረው ሪፎርም በኋላ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር እንዳይወስድ መደረጉን የኮሚቴው መግለጫ አስታውሷል።

ይህም የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በማገዝ እና የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትን በመገደብ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል።

በዚህ የተጠናከረ የፖሊሲ እርምጃ ምክንያት 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 10 ወራት አጠቃላይ የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ምጣኔ ወደ 0.9 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተገልጿል።

ይህ አኃዝ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 1.6 በመቶ እንዲሁም ከሪፎርሙ በፊት 2016 ከተመዘገበው 2.1 በመቶ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ጉልህ የሆነ ቅናሽ የታየበት ነው።

ከብሔራዊ ባንክ የሚወሰደው ብድር በመቆሙ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ገበያን በቁልፍ አማራጭነት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ነው ኮሚቴው የጠቀሰው።

ይህ የፋይናንስ ሥርዓት ለበጀት አፈፃፀሙም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሶ፣ 2018 በጀት ዓመት በዚሁ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ አማካኝነት 206.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የኮሚቴው መግለጫ አብራርቷል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: