ሀገር ማለት ከቁሳዊ ግንባታዎች ባሻገር በዓይን የማይታዩ ነገር ግን የኅልውናዋና የጽናቷ ዋነኛ ምሰሶ የሆኑ እሴቶች፣ ባህሎች፣ ተቋማትና ሥነ-ልቦናዊ ትስስሮች ድምር ውጤት ናት።
እነዚህን ረቂቅና መሰረታዊ የሀገር ግንባታ አካላት ደግሞ “ሱፕራና አልትራስትራክቸር” (Supra and Ultra-structure) በማለት ልንጠራቸው እንችላለን።
ሱፕራ-ስትራክቸር አንድ ማኅበረሰብ በጋራ ሊመራባቸው የሚገቡ ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፎችን የሚፈጥር ሲሆን፣ አልትራ-ስትራክቸር ደግሞ ከሱፕራ-ስትራክቸር የበለጠ ጠቅለል ያለ በማኅበረሰቡ የሥነ-ልቦና መዋቅር ውስጥ የገባው ረቂቅ ካፒታል ነው።
እሱም ሕዝቡ በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚተገብራቸው ባህሎች፣ የጋራ ትውፊቶች፣ የሞራል እሴቶች፣ የማይታዩ ሥነ-ልቦናዊ ትስስሮች፣ የአብሮነትና የመቻቻል መንፈሳዊ እምቅ አቅሞች ናቸው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአካላዊ ልማት፣ በታላላቅ የከተማና የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንዲሁም በሰፊ የጂኦፖለቲካዊ ሽግግር ውስጥ በምታልፍበት በዚህ ወሳኝ እና ታሪካዊ ምዕራፍ፣ ይህንን ረቂቅ የሀገር ግንባታ ሚስጥር ጠልቆ መገንዘብና መፈተሽ ያለው ፋይዳ በእጅጉ የላቀ ነው።
ይህንን እውነታ በማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ የሀገር ግንባታን ሁለንተናዊና ሁለገብ ባህሪ በስፋት ሲያብራሩ ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ሀገር መሆኗንና ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ውስጥ በጣም አስፈላጊና ስር የሰደደ ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ አስገንዝበዋል።
ሀገር በኢንፍራስትራክቸርና በአካላዊ መዋቅር ብቻ በፍፁም ሊገነባ እንደማይችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሱፕራና አልትራስትራክቸር ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ደኅንነት በእጅጉ እንደሚያስፈልግና እነዚህን ረቂቅ መዋቅሮች የሚገነቡ ባህሎች፣ ትውፊቶች እና እሴቶች ለኢትዮጵያ ቀጣይነትና አንድነት ወሳኝ መሆናቸውን በጥብቅ አሳስበዋል።
ይህ ማብራሪያ በግልጽ እንደሚያመላክተው፣ ሀገርን በአካላዊ መሠረተ ልማት እና በቁሳዊ እድገት ብቻ የመገንባት እሳቤ ሰብአዊና ማኅበራዊ እሴቶችን ሙሉ በሙሉ ችላ የማለትና የመርሳት ከፍተኛ አደጋ አለው።
ማኅበራዊ ትስስሯ፣ የጋራ ሞራላዊ እሴቶቿና ተቋማዊ ጥንካሬዋ በአግባቡና በትክክለኛው መሠረት ላይ ያልተገነባ ሀገር፣ የቱንም ያህል ታላላቅ መሰረተልማቶች ቢኖሯትም እንኳ በቀላል የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም በማኅበራዊ ቀውስ ፈጥና ልትናጋ የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
ስለዚህ ሱፕራና አልትራስትራክቸር የሚባሉት ይኸውም ሕዝብን በጋራ አስተሳስረው የሚያቆሙ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች፣ የጋራ ትርክቶች፣ ማኅበራዊ ስምምነቶችና ተቋማዊ ህጎች ለሀገር ዘላቂ ኅልውና እንደ ዋና መከላከያ ጋሻና ምሰሶ ሆነው ያገለግላሉ።
በኢትዮጵያ ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ይህንን ሱፕራ-ስትራክቸር የሚቀርጸውና ሕዝቡን በችግር ጊዜ ጭምር በትስስር የሚያቆየው ዋናውና አንቀሳቃሹ ምሰሶ ሃይማኖት ነው።
የሀገራችን የረጅም ዘመን ታሪክና ማኅበራዊ ጉዞ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ሃይማኖት በተለያዩ እምነቶች መካከል ልዩነቶችን አጥብቦ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የፍቅር እና የአብሮነት እውነተኛና ዘላቂ ምንጭ ሆኖ ነው የኖረው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ አብዛኞቹ ግጭቶችና ጦርነቶች መነሻዎቻቸው ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ርዕዮተ-ዓለም፣ የኢኮኖሚ የበላይነት ፍላጎት እና ግዛት ማስፋፋት እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል።
ነገር ግን የነገሩ እውነተኛ ገጽታ ሲመረመር እነዚህ አደገኛ የኢኮኖሚ ጥቅምና የስልጣን የበላይነት ፈላጊዎች ራሳቸውን በረቀቀ መንገድ በመደበቅ፣ የሃይማኖትና የብሔር ስሜታዊ ካባን በማልበስ ለራሳቸው የግጭትና የፖለቲካ ቁማር መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እውነተኛውና መሬት ላይ ያለው ማኅበራዊ ገጽታ ከዚህ ጊዜያዊ የፖለቲካ ቁማርና አጀንዳ በእጅጉ የላቀና የጠነከረ ጥልቀት ያለው ነው። ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለክርስቲያኑ ቤተክርስቲያን ግንባታ፣ ክርስቲያኑም እንዲሁ ለሙስሊሙ መስጂድ ግንባታ በገንዘብና በጉልበት አብሮ የሚቆምባት፣ አንዱ ከሌላው ጋር የሚደጋገፍባት ልዩ ሀገር ናት።
ማኅበረሰቡ እርስ በእርሱ የሚተሳሰረው ሰፊ በሆኑ የጋራ እሴቶች፣ ባህሎችና ሥነ-ልቦናዊ ትስስሮች ሲሆን፣ በመካከሉ ያሉት ጥቂትና ትናንሽ ልዩነቶች መስተጋብሩን በፍፁም አያናጉትም።
በመሆኑም ይህንን እምቅ ባህላዊና መንፈሳዊ ካፒታል ወይም አልትራስትራክቸርን በጥንቃቄ መያዝ፣ ማልማት እና ማጠናከር፣ ሀገርን ከውስጥ ከሚነሱ የመከፋፈል አደጋዎች ይጠብቃል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: