የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የሀገራችንን ወቅታዊ ጉዳይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሐሳብ አንስተዋል።
ከሚሽነሩ፣ "በውስጥ ያለን ሰዎች ሕልውናችንን ካልጠበቅን፣ ካልተነጋገርን እና ካልተመካከርን ሕልውናችን ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል" በማለት ነው ሐሳባቸውን የሰነዘሩት።
ይህ ሐሳብ የውስጥ አንድነት እና የጋራ መግባባት ለአንድ ሀገር ሕልውና መሠረታዊ ዋስትና መሆናቸውን በግልጽ ያረጋግጥልናል።
በውስጥ ያሉ ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት ባህል ማዳበር ካልተቻለ የውስጥ ድክመቶች ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እና ለታሪካዊ ጠላቶች ጥቃት በር እንደሚከፍቱ የፖለቲካ ምሁራንም አጥብቀው ይስማማሉ።
በመሆኑም የውጭ ጫናን ለመቋቋምና የሀገርን ሕልውና ለማስጠበቅ የውስጥ አቅምን መገንባት መሠረታዊ መፍትሔ መሆኑ አያጠያይቅም።
የውስጥ ምክክርና መግባባት ከሌለ የሀገርን ሕልውና በዘላቂነት ማስጠበቅ አይቻልም። ሀገራዊ ምክክሮች የፖለቲካ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
ይህንን የሕልውና ስጋት እና የምክክርን ፋይዳ በሚገባ የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሠረቱ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ጀምሮ የተገነባ እና ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ታሪካዊ የብሔራዊ ምክክር ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቅድመ ዝግጅት፣ የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል።
የዚሁ ታሪካዊ ሂደት ትልቁ ማሳያ የሆነው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤም ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።
ለዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ስኬታማነት ከመላው የሀገራችን ማዕዘናት የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ስለ ውይይት ሥነ ምግባር እና የአሠራር ሥርዓትም ሰፊ የቅድመ ምክክር ገለጻ እና ሥልጠና ተሰጥቷቸው ዝግጁ ሆነዋል።
በዚህም መሠረት በተለዩት ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ በጉባኤው ተሳታፊዎች ምክክር ተደርጎ ለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል የሚጠቅሙ ሐሳቦች ነጥረው ይወጡበታል፡፡
ይህ ጉባኤ የተጣለበትን ሀገራዊ አደራ እንዲወጣ እና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም አካል የድርሻውን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።
የሐሳብ ልዩነቶችን በጦርነት ሳይሆን፣ በውይይት መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ ወገኖች መኖራቸውም ለሂደቱ ትልቅ ተስፋ ነው።
የኢትዮጵያ የሕልውና ዋስትና የሚወሰነው በውስጥ ኃይሎች መነጋገር፣ መደማመጥ እና መጠራጠርን ማስወገድ ላይ መሆኑን በመገንዘብ ለመላው ሀገራችን የተዘረጋውን ይህን ትልቅ ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ጽኑ መሠረት እንዲጥል እና የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ሰላም እንዲያረጋግጥ በመንግሥት በኩል በምክክሩ የሚደረሱ መግባባቶችን በተግባር ለመተርጎም ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል።
የሀገር ግንባታ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ይህን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለምክክሩ ስኬት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: