Search

እነሆ ኢትዮጵያ መምከር ጀምራለች

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 147

ለዘመናት በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቡድኖች፣ ግለሰቦች፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች እና የተለያዩ ጠባብ የጥቅም ቡድኖች የራሳቸውን ፖለቲካዊ ምኞት እና ግላዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ ኢትዮጵያን ከእውነተኛ ምክክር እና ከሠለጠነ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አርቀዋት ኖረዋል።

የራሳቸውን አጀንዳ በሕዝብ ላይ ለመጫን ሲሉ የሐሳብ ሙግትን በጠብመንጃ ሲደፈጥጡ፣ የሕዝብን ድምፅ ሲያፍኑ እና ወንድም በወንድሙ ላይ ጦር እንዲያነሳ ሲያደርጉ ሀገራችንን ክፉኛ አድምተዋታል። ነገር ግን ይህ የጨለማ፣ የሴራ እና የመጠፋፋት ዘመን ዛሬ በይፋ አክትሟል።

ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ አፋኝ እና ከፋፋይ ኃይሎች፣ የግለሰቦችን ግትር ፍላጎት ወደ ጎን ገፍታ፣ ሁሉንም ተቃርኖዎች አሸንፋ በልጆቿ ብርቱ ጥረት እና ጽናት እነሆ ዛሬ ታሪካዊውን መመካከር በይፋ ጀምራለች።

ይህ በዛሬው ዕለት የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ በደማቅ ወርቃማ ቀለም የሚጻፍ፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፈትበት እና አዲስ ሀገራዊ እውነት የሚመዘገብበት ብሩህ ማለዳ ነው። በዚህ ማለዳ የትናንቱ የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ የነገው የተስፋ ድልድይ መገንባት ጀምሯል።

ኢትዮጵያ ዛሬ የምክክርን እውነት፣ የልጆቿን በአንድነት መመካከር እና የሠለጠነ የሐሳብ ልዕልናን ማሸነፍ በአደባባይ እያወጀች ትገልጣለች።

የኢትዮጵያ ልጆች ከተመካከሩ፣ ከተደማመጡ እና በእውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ ከተባበሩ ሊሠሩት የሚችሉት ተአምር፣ ሊደርሱበት የሚችሉት የሥልጣኔ ማማ ወሰን የለውም።

አባቶቻችን እና እናቶቻችን ተባብረው እና ተመካክረው አስደናቂውን የአክሱም ሐውልት ከጠንካራ አለት እንዳቆሙ፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጥበብ እንዳነጹ እንዲሁም በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ የሀገራችን ክፍሎች ዓለምን ያስደመሙ ታላላቅ እና አኩሪ ሥልጣኔዎችን እንዳኖሩ ሁሉ፤ ዛሬም እናንተ ልጆቻቸው በሠለጠነ ጠረጴዛ ዙሪያ ባደረጋችሁት ታሪካዊ የምክክር ውሳኔ አዲስ የሕዳሴ እና የብልጽግና ምዕራፍ ትከፍታላችሁ።

የትናንት አባቶቻችን በድንጋይ ላይ ብሩህ ታሪክ እንደሠሩት ሁሉ፣ የዛሬዎቹም የኢትዮጵያ ልጆች አሮጌውን የስብራት ታሪክ ሽረው በሐሳብ እና በመግባባት ላይ ጸንቶ የሚቆም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይከፍታሉ።

ይህ የዛሬው መመካከር የፖለቲካ ስብራታችንን ጠግኖ፣ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ መግባባትን በጽኑ መሠረት ላይ ለማስፈን የተዘረጋ ታላቅ የትውልድ ድልድይ ነው።

መለያየትን ወደ አንድነት፣ ቁርሾን ወደ ይቅርታ በመቀየር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሞ የማይናወጥ፣ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የሚያቅፍ፣ ብዝኃነትን የሚያከብር እና በሕግ የበላይነት የሚመራ ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት ዛሬ የማይናድ የመሠረት ድንጋይ ይጣላል።

የዜሮ ድምር ፖለቲካ አክትሞ፣ የጠብመንጃ አፈሙዝን የሠለጠነ የጠረጴዛ ውይይት ተክቶት፣ እውነተኛ የትብብር እና የመግባባት ዴሞክራሲ እውን የሆነበት ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ፣ የዘመናት ስብራታችን የተጠገነበት ተብሎ ትውልድ ሲያልፍ ትውልድ ሲተካ በታላቅ ክብር ሲዘከር የሚኖር ደማቅ የድል ታሪክ ነው።

ኢትዮጵያ መመካከር በመጀመሯ አሸንፋለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: