በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ አገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንደጠቆሙት፣ አንዳንድ አጋጣሚዎች የሰው ልጆችን ከታሪክ ብዕርና ብራና ፊት ያቆሟቸዋል።
በዚህ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ መቆም ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የሚቀጥል ታሪክን በገዛ እጃችን እንድንጽፍ እድሉ ተሰጥቶናል።
ዛሬ የምንገኝበት የሀገራዊ ምክክር መድረክ ልባም ለሆኑ ሰዎች፣ የታሪክን፣ የአጋጣሚንና የእድልን ታላቅነት ለተገነዘቡ ዜጎች የተከፈተ የጋራ ምዕራፍ ነው።
ይህ መድረክ ሀገርን የሚታደግ፣ የሚጠቅም እና ለዘመናት የሚታወስ በጎ ታሪክን እንድንጽፍ የሚያስችለን ወርቃማ አጋጣሚ መሆኑን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ይህንን የታሪክ እድል በሚገባ መጠቀም ያልቻሉ አካላት፣ ብዕርና ብራና ቢሰጣቸውም እንኳን ሀገርን ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርስ፣ ከሚያበለጽግ ይልቅ የሚያደኸይ እና ስብዕናን የሚያጠብ ታሪክ ጽፈው እንደሚያልፉ ተናግረዋል።
ያ ቀደም ሲል የነበረ መጥፎ የታሪክ ምዕራፍ ዛሬ በእኛ ዘመን እንዳይደገም ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰማን እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እኛና ከእኛ በፊት የነበሩት ሰዎች ያጧቸውን፣ ሊያሳኳቸው ሲገቡ ያልቻሏቸውን የሀገር ግንባታ ምዕራፎች ዳግም ልጆቻችን እንዳያጡ በአደራና በኃላፊነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በብዕራችን የምንጽፈው ታሪክ ለሀገር ግንባታ የሚጠቅም፣ ትውልድን የሚያበለጽግ እና ኢትዮጵያን ለዘመናት የሚያሻግር እንዲሆን ሁላችንም በጋራ መትጋት እንዳለብን አስገንዝበዋል።
ታሪክ በብዕራችን እንድንጽፈው እድል በሰጠን በዚህ ታላቅ ወቅት፣ ለሀገር የሚተርፍ አሻራ ለማሳረፍ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: