በታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የምክክሩ ስኬት ሙሉ በሙሉ የሚረጋገጠው እርስ በርስ በመደማመጥ እና የሁሉንም ወገን ጥያቄዎች በአክብሮት በማስተናገድ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገር የሚበጅ የጋራ መፍትሔ ለማምጣት የአፋር አባቶችን ጥበብ ማስታወስ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ “አንድ ቦታ ላይ ተቀምጠህ በሌላኛው ወገን ያለውን ችግር መረዳት ስለማትችል፣ ተነስተህ ሂድና ያኛው ወገን ምን እንደሚያስብ፣ ምን ጥያቄ እንዳለው አድምጥ” የሚለውን ምክር በተግባር መተርጎም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን ማጽናት የሚቻለው ሁሉንም ድምፆች እኩል በማድመጥ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በቁጥር ሰፊ የሆኑት የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች የሌሎችን ወንድሞቻቸውን ጥያቄዎች ማድመጥ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
"ዳሰነችን፣ ኮንሶን፣ አሌን ካላደመጣችሁ ኢትዮጵያን ልታጸኑ አትችሉም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቁጥር ትልቅ የሆኑ ወገኖች ሌሎችን ካላከበሩና ፍላጎታቸውን በቁጥር የበላይነት ብቻ ለመጫን ከሞከሩ ውይይቱ እንደማይሳካ አስጠንቅቀዋል።
ምክክሩ ፍሬያማ የሚሆነው አንዱ ወገን የሚያነሳው ጥያቄ ሌላውን የማይጎዳ መሆኑን እያረጋገጡ በጋራ ለመጠቀም መስማማት ሲቻል እንደሆነ እና "ለእኔ ሳይሆን ለእኛ፣ ለሰፈሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ" ማለት ሲቻል ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በትግራይ አባቶች ዘንድ “የአንድ ሰው ምክር ከምድር በታች ነው፣ የሁለት ሰው ምክር ከምድር በላይ ነው፣ የሦስት ሰው ምክር ግን ምርጥ ዘር ሆኖ ይበቅላል” የሚባል ታላቅ ምሳሌ እንዳለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ታላቅ የውይይት ባህል በመጠቀም የተሰበሰቡት ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች አዕምሮአቸውንና ልባቸውን በአዳራሹ ውስጥ ሰብስበው ሌላኛውን ወገን ማድመጥ ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም፣ ይህ ታሪካዊ መድረክ የ130 ሚሊዮን ዜጎች እና የመቶዎች ሚሊዮን የነገ ትውልድ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ተሳታፊዎች በጉባኤው ውስጥ በትጋት በመሳተፍ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እረፍት እና ዘላቂ ሰላም የሚሰጥ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አደራ ብለዋል።
በማስተዋል መታፈሪያ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: