ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን የተደረገችበት ዋና ምክንያት የውስጥ መከፋፈል ሴራ እና ስንፍና መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ለሺሕ ዘመናት በባለቤትነት ይዛ የቆየችውን ቀይ ባሕር ያጣችበት አጋጣሚ፣ ከውጭ ጠላት ጥቃት ይልቅ በውስጥ መዘናጋት እና አንድነት መጥፋት የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
እርሳቸው እንደገለጹት፣ ያልተመረጠ እና ያልተወያየ መንግሥት በሸፍጥ ኢትዮጵያን ከባሕር መውጫዋ እንድትነጠል ያደረገው የውስጥ ድክመትን ተጠቅሞ ነው።
ይህ ታሪካዊ ክስተት እንደ አንድ እኩይ እሳቤ መገለጫ የሚጠቀስ መሆኑን አንሥተው፣ “የኢትዮጵያን መሻት እና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል የለም፤ ያልተሳካልን በውስጥ ስንፍናችን እንጂ አቅም አጥተን አይደለም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት የኖረች እና የምትኖር የጸናች ሀገር መሆኗን በማስታወስ፣ ጥቅሟን አሳልፎ ለመስጠት የሚደረጉ ሙከራዎች በውስጥ መከፋፈል የሚመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ የሚታዩ ፕሮፓጋንዳዎች እና የውስጥ አለመግባባቶች ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የባሕር ተጠቃሚነት ለማግለል የሚደረግ ሴራ አካል መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ሕዝቡ በአንድነት እና በጋራ መግባባት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መቆም እንዳለበት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: