የተለያዩ አመለካከቶች የማንነታችን እና የዴሞክራሲያዊ ሕይወታችን አካልም ውበትም መሆናቸውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል፡፡
የሐሳብ ልዩነቶች በራሱ ችግር አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ እነዚህን የሀሳብ ልዩነቶች ግን የሚያለያዩን መሆን እንደሌለባቸው አስምረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
የተከማቹ እና ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ እና የሥራ ጥያቄዎች በመካከላችን የሚታዩ አለመግባባቶች እና ቅራኔዎች ዛሬም ድረስ የዜጎችን ሰላምና የሀገር አንድነትን አየፈተኑ ይገኛል ብለዋል።
የሐሳብ ልዩነቶች በራሱ ችግር አይደለም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የተለያዩ አመለካከቶች፣ የማንነታችንና የዴሞክራሲያዊ ህይወታችን አካል ናቸው፤ ውበትም ናቸው ብለዋል።
ችግር የሚሆነው እነዚህን ልዩነቶች በምክክር ፈንታ በግጭት፣ በመገለል እና በኩርፊያ ወይም በኃይል ለመፍታት ሲሞከር ነው ሲሉም አመልክተዋል።
እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮቻችን በኃይል፣ በጊዜያዊ ማስታገሻዎች ወይም በአግላይ ሂደቶች በዘላቂነት መፍታት እንደማይቻል ታሪካችን አስተምሮናል ነው ያሉት።
ምክክር ብዝኃነታችንን የሚያጠፋ ሳይሆን፣ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ ይዘን በጋራ መኖር የምንችልበትን ሥርዓት የምንዘረጋበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።
ዛሬ የሚጀመረው ጉባኤ እርስ በእርሳችን እንድንደማመጥ፣ የሌላውን ህመም እንድንረዳ፣ በየጊዜው የሚያመረቅዙ ትርክቶችን እና የታሪክ ጠባሳዎችን እንዲሽሩ ለማድረግ በጋራ የወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ እንድንስማማ ዕድል የሚሰጥ ሀገራዊ ፈውስ የምናካሂድበት ነው ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: