Search

“ታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ እርምጃ የሚደመደመውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ አዙሪት የሚሰብር ነው”፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 103

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ መድረኩ ኢትዮጵያ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ እርምጃ የሚደመደመውን የፖለቲካ አዙሪት በመስበር በንግግር እና በውይይት የምትተካበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ እንድትጽፍ የሚያስችላትን ብዕር እና ብራና ያገኘችበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

መድረኩ በቀጣዮቹ ሳምንታት አራት ሺህ ተሳታፊዎችን በአንድ ጣሪያ ሥር የሚያሰባስብ መሆኑን በማንሣት፣ ሂደቱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ከታች ወደ ላይ በዘለቀ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዞ መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ይህ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ግዙፍ እና ታላቅ ዓላማ ያለው ጉባኤ፣ ሀገራችን የገጠሟትን ፈተናዎች ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ባህልን ለማጽናት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

ዛሬ የሚዘራው መልካም ዘር ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ እና ልጆች ፍሬውን የሚቋደሱት መሆኑንም አክለዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች ከሰፈር አስተሳሰብ ወጥተው ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ መጪው ትውልድ በማሰብ ፍሬያማ ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገራዊ ችግሮችን በውስጥ ውይይት እና በይቅርታ መፍታት ሀገርን ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚታደግም በመጠቆም፣ የምክክሩ ውጤት ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ስኬት እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: