Search

“ለታሪክ የተጻፈ ውለታ!” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለኮሚሽነሮቹ የሰጡት ታሪካዊ ክብር

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 139

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት አራት ዓመታት በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈው ጉባኤውን ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ያደረሱትን የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን በጀግንነት ሥራቸው አመስግነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኮሚሽነሮቹ እንደወረደባቸው የዱላ ውርጅብኝ ሳይበገሩ በጽናት መፋለማቸውን በመጥቀስ፣ ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ መዋላቸውን ተናግረዋል።

እንደወረደባችሁ ዱላ ባትገኙ ነበር፤ ተቋቁማችኋል ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ በጀግንነት የተሞላ አደራ የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የነገውም ትውልድ በክብር የሚያስታውሰው ታሪካዊ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ አባላት የሠሩት ሥራ ለሀገር ብልጽግናና ዘላቂ ሰላም መሠረት የሚጥል መሆኑን በመጥቀስም፣ ጊዜያቸው ያማረ እና ለትውልድ የሚተርፍ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ጸሎት ያደረጉትን የሃይማኖት አባቶች በማድነቅ፣ አባቶቹ ሀገራቸውን የሚወዱ እና ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወይም የብሔር የተደበቀ ዓላማ የሌላቸው ምርጥ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ አባቶች ከጉባኤው ሲመለሱም በየቤተ እምነታቸው ለተወያዮቹ ልቦና፣ ማስተዋልና ፍቅር እንዲሰጣቸው በጸሎት እንዲያስቧቸው የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህ የአባቶች ጸሎት እና የኮሚሽነሮቹ የማይናወጥ ጀግንነት ለኢትዮጵያ አንድነት እና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በጌቱ ላቀው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: