Search

ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል በራሷ የመፈወስ አቅም አላት - ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 116

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (/) በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ለመጻፍና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል መፈጠሩን ገልፀዋል።

ዋና ፀሐፊው በንግግራቸው ጉባኤው ትልቅ ታሪካዊ ሁነት ከመሆኑ ባለፈ በኢትዮጵያ ረጅም እና አኩሪ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚጻፍበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት እና በጦርነት የተገነባ ሀገር አለመኖሩን የጠቀሱት / ወርቅነህ፣ ዛሬ ላይ የሰለጠኑት እና የበለፀጉት ሀገራት ለዚህ ደረጃ የበቁት ለሀገራቸው ቅድሚያ በመስጠት እና በውይይት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ማንነቷን የምትፈልግ አዲስ ሀገር ሳትሆን በጥንታዊ እና በጠንካራ ሥልጣኔዎች ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትመደብ ታላቅ ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ በባሕሏ እና በሃይማኖቷ ሥር የሰደዱ እና ውብ የሆኑ የዕርቅ እና የሰላም ሥርዓቶች እንዳሏት አስታውሰው ያሏትን ባህላዊ የዕርቅ እሴቶች የሀገር ሽማግሌዎች በጥበብ በተቃኘ መንገድ የሀገርን ቁስል በራስ መንገድ ማከም የሚችሉበት ቁልፍ በእጃቸው እንደነበረ አስታውሰዋል።

በቀደሙት ዘመናትም ቢሆን ለጥያቄዎች ምላሽ ፍለጋ ወደ ውጪ የማማተር ልምድ እንዳልነበረ በመጠቆም፣ አሁንም ወደ ውስጥ መመልከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ ዕለት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ የሚስተናገድበት መሆን እንዳለበት የገለጹት / ወርቅነህ፣ "ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በብዕር ኃይል፣ በውይይት እና በጋራ መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ከሁሉ በላይ ለራሳችን የምናስመሰክርበት ዕለት ነው" ብለዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች የሚወክሉትን ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ በአንክሮ ማሰብ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ዋና ፀሐፊው፥ ግጭቶች በአስቸኳይ ሊያበቁ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: