ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እየተካሄደ ያለውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የተረሳውን የኢትዮጵያውያን የጋራ ምክክር ባህል ወደ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ምንም እንኳን ሕዝቡ ልሂቃን በሚፈጥሩት ግጭት ሲታመስ ቢቆይም፣ የኢትዮጵያውያን መሠረታዊ ባህል ግን ለምክክር ያደላ መሆኑን አንሥተዋል።
ይህንን ለማሳየትም ቤቶች፣ መሶቦች፣ አቀማመጦች እና ማብሰያዎች "ክብ" ቅርጽ ያላቸው መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰው፣ ይህም ነገሮችን ሰብሰብ ብሎ በመመካከር ለመከወን እንዲያመች ታስቦ የተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የክብ ቅርጽ መነሻ እና መድረሻ፣ ሩቅ እና ቅርብ እንዲሁም ወጪ እና ገቢ የሌለው በመሆኑ ሁሉንም ማኅበረሰብ በእኩልነት እንደሚያሳትፍ አብራርተዋል።
ይህንን የቆየ እና የተረሳ ባህል ወደ አሁኑ ሀገራዊ ምክክር ማምጣት መቻሉን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን መጥተው በጋራ እየመከሩ እንደሚገኙ እና በሂደቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ለሆነ ሁሉ ዕድል መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በገዛ ልጆቿ ለነገ እንድትሆን ተደርጋ ልትገነባ መሰባሰቧን አስገንዝበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክክሩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ "የሀገር ጸሎት፣ ልብ እና ጆሮ ከእናንተ ጋራ ነው" በማለት ሀገራችን በጉባኤው ላይ ያላትን ትልቅ ተስፋ እና ትኩረት ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: