Search

የሀገራችን ባሕል ከዋርካ ዛፍ ጋር በፅኑ የሚቆራኝ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 122

ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያውያን ባህል ላይ የሚንተራስ ከሆነ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን፣ ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የሚዘልቅ ጽኑ መሠረት መጣል የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያውያን ከባህላችን፣ ከማንነታችን እና ከታሪካችን ሳንነጠል በራሳችን ፈቃድና ደስታ እንዲሁም በኃላፊነት ስሜት ውይይቱ የሚካሄድ ከሆነ ልጆቻችን የበለጸገችና የጸናች ሀገር መረከብ ይችላሉ ብለዋል።

የሀገራችን ባሕል ከዋርካ ዛፍ ጋር በፅኑ እንደሚቆራኝ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "በዋርካ ሥር ለሽምግልና እንቀመጣለን፣ ለትዳር በሽምግልና እንጠይቃለን፣ የሃይማኖት ትምህርቶችን እንማራለን፣ በዋርካ ሥር አባቶች ዘር ያስቆጥሩናል፣ እንማማራለን እንዲሁም በሥሩ እናርፋለን" ሲሉ የዛፉን ማኅበራዊ እና ባህላዊ ፋይዳ አስረድተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ዋርካን የመቁረጥ አዝማሚያ ተስፋፍቶ እንደነበር አንስተው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም በመካከላችን የነበረው የምክክር ባህል እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል።

"አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ" መባባሉ ቀርቶ ከእኔ ወዲያ ማን እና እኔ ያልኩት ካልሆነ ወደሚል አደገኛ ልምምድ ተቀይሮ እንደነበር አመላክተዋል።

ተስፋን እንተከል በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራም ከዛፍ ባሻገር ውይይትን፣ ይቅርታን እና በጋራ መቆምን የማፅናት ዓላማን ያነገበ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ለሰፈር ወይም ለወገን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብላችሁ እንድትመክሩ አደራ እላለሁ ሲሉም ለጉባኤው ተመካካሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: