በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ቀጣና ጭምር ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።
ልዩ መልዕክተኛው በታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሒደት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቀረፁት የሰላም ራዕይ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በናይጄሪያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያሉትን በርካታ ታሪካዊ መመሳሰሎች ያነሡት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ከውጭ ጠላት ጋር ከመዋጋት እጅግ የከበደ መሆኑን አብራርተዋል።
በውጭ ጦርነት ውስጥ ግልጽ አሸናፊ ሊኖር ቢችልም፣ በሀገር ውስጥ ግጭት ግን ማኅበረሰቡን መልሶ አንድ ላይ ለማያያዝ እጅግ ውስብስብ ጥረት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።
ናይጄሪያ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ማብቃት በኋላ ካለፉት ግትር ፖለቲካዊ አቋሞች በመውጣት "ማንም አሸናፊ፣ ማንም ተሸናፊ የለም" የሚል ፖሊሲ በመቅረጽ የጋራ የእርቅ ጉዞ መጀመሯን ያስታወሱት ልዩ መልዕክተኛው፣ ይህንን ተሞክሮ በማጣቀስ አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክርም የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል።
በተያያዥም ልዩ መልዕክተኛው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የስንዴ አቅርቦት እጥረት በተከሰተበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመት በፊት "ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ትችላለች" ሲሉ የገቡትን ቃል በተግባር በማሳየታቸው የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ራሷን ችላ ለሌሎች ሀገራት ጭምር መትረፍ መቻሏንም አድንቀዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: