የሰው ልጅ የሕይወት ጉዞ እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚስጥር የሚፈታው የጊዜን እና የቦታን ጥልቅ ቀመር በውል መረዳት ሲቻል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገራዊ የምክክር መድረክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር፣ "ከታሪክ ብራናና ብዕር ፊት ቆማችኋል" ሲሉ ያስተላለፉት መልእክት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በስፋት ካነሱት የ'ጊዜና ቦታ' ፍልስፍና ጋር ተዳምሮ ሲታይ እጅግ ረቂቅ የሆነ ሀገራዊ እይታን ይፈጥርልናል።
ታሪክ እና ብራና ልክ እንደ ጊዜ እና ቦታ በኢትዮጵያውያን የሥነ-ቃል ጥበብ ውስጥ እንደሚገኘው የ'ሰምና ወርቅ' ቅንብር ናቸው።
አንዱ የወርቁን ሚስጥር አቅፎ የያዘ ሰም ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የሰሙን ማዕቀፍ ሰንጥቆ የሚወጣ አንጸባራቂ ወርቅ ነው።
አንዱ የአንዱን ጥልቅ ሚስጥር አጉልቶ ይገልጻል። ጊዜ ኃላፊ ነው፤ ጊዜ ፈጣን፣ ተጓዥ እና ወደ ኋላ የማይመለስ የሕይወት ጅረት ነው።
ቦታ ደግሞ ይህ ተጓዥ ጊዜ ዕረፍት የሚያገኝበት፣ ታላላቅ ክንውኖች የሚፈጸሙበት እና የሰው ልጅ ጥበቡን የሚያሳይበት ሰፊ ዐውድማ ነው።
ጊዜ የቦታን፣ የድርጊትን፣ የማሸነፍን እና የመከናወንን ዕድል አቅፎ ሲመጣ፣ ቦታ ደግሞ ያንን ረቂቅ ዕድል ወደ ተጨባጭ ተግባር ይቀይረዋል።
የጊዜ እና የቦታን ሚስጥር ያወቁ፣ ጥልቅ ስሌቱን የተረዱ ሀገራት እና ትውልዶች ዛሬ በዓለም ላይ በስኬት ማማ ላይ ተቀምጠዋል።
የራሳቸውን ዘመን፣ የተሰጣቸውን ዕድል፣ እና ያሉበትን ቦታ አመጣጥነው የተጠቀሙ ሕዝቦች ታላላቅ ሥልጣኔዎችን በየዘመናቱ አኑረዋል፤ ታሪክን ሠርተው በክብር ተሻግረዋል።
የጊዜ እና የቦታ መገጣጠም ከፍተኛው ውጤት "ታሪክ" ነው። ይሁንና ታሪክ የቱንም ያህል ገናና ቢሆን ያለ ብራና ዋጋ የለውም፤ ብራናም የቱንም ያህል ውድ ቆዳ ቢሆን ያለ ታሪክ ባዶ ነው።
ታሪክ ክንውንን ይሠራል፤ ብራና ግን ያንን የተሠራውን ታሪክ በብዕር ቀለም ተቀብሎ ቆንጥጦ ይይዘዋል።
ብራና ታሪክን ከመረሳት አደጋ ይታደጋል፤ ለትውልድ ያሻግረዋል፣ ዘመን ተሻጋሪ እና ሕያውም ያደርገዋል።
ጊዜም ያለ ቦታ፣ ቦታም ያለ ጊዜ ትርጉም እንደሌላቸው ሁሉ፣ ታሪክ እና ብራናም የማይነጣጠሉ፣ በገመድ የተሰናሰሉ ሰምና ወርቆች ናቸው።
ታሪክ የጊዜን ማኅፀን ሰንጥቆ ሲወጣ፣ ብራና ደግሞ የቦታን ትዕግሥት ወክሎ ያንን ታሪክ በክብር ያሰፍረዋል። የሁለቱ ቁርኝት የትውልድን ዕጣ ፈንታ የሚወስን እጅግ ረቂቅ የሆነ የሕይወት ሚስጥር ነው።
ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ታሪክ እና ብራና በአዲስ መልክ የሚቀያየሩበት ጊዜ እና ቦታ ቃል ኪዳን የሚያስሩበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ቆመናል።
ትውልዱ አዲስ ታሪክ እየጻፈ ነው፤ የዘመኑ ብራናም ይህንን የሰላም፣ የዕድገት እና የውይይት ሐሳብ በደማቁ እያሰፈረው ይገኛል።
የተሰጠንን ዕድል ተጠቅመን፣ ጊዜውን ተረድተን ቦታን መለየት ጀምረናል። "ቦታው የት ነው?" ብለን ብንጠይቅ—ቦታው በየዕለቱ አዲስ ውበቷ እየተገለጠች ያለችው ታላቂቱ ኢትዮጵያ ናት።
ቦታው፣ ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን፣ የእርሻ፣ የማዕድን እና የቱሪዝም ጸጋዎቻችንን በዕውቀት መለየት የጀመርንበት ሰፊው ምድራችን ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ቦታው፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ የትናንት ስብራቶቻችንን ጠግነን በጠረጴዛ ዙሪያ 'መመካከር' የጀመርንበት ታሪካዊው የአደባባይ ሸንጎችን ነው።
አሁን ጊዜ እና ቦታ በአንድ ማዕከል በእርግጥም ተገናኝተዋል። በዚህ ወርቃማ የታሪክ አጋጣሚ ትውልድ እና ሕዝብ በአንድ ዓላማ ተገናኝተዋል።
የዛሬው ትውልድ የተሰጠውን ልዩ ዕድል አውቋል፤ ጊዜን ነቅቶ በመጠበቅ ቦታን በአግባቡ ለይቷል።
ያልተጻፈበትን ንጹሕ ብራና አግኝቶ፣ በሚያኮራ ሀገራዊ ተግባር አዲስ ታሪክ እየጻፈበት ይገኛል። የታሪክ እና የብራና ሰምና ወርቅ ተገጣጥሟል።
የጊዜና የቦታ ሒሳብ በትክክል ተሰልቷል። ዛሬ ኢትዮጵያ በልጆቿ የነቃ ምክክርና አብሮነት፣ በማይሽረው የዘመናት ብራና ላይ፣ ነገን የሚያሻግር እና ዓለምን የሚያስደምም አንጸባራቂ ታሪክ እያሰፈረች ነው።
ይህ ጊዜ ኢትዮጵያ ታሪኳን አድሳ በተግባር ብራና ላይ የምታትምበት፣ የልጆቿ ምክክር እና ጥረት ሰሙን ገልፎ ወርቁን የሚያወጣበት እጅግ ብሩህ ዘመን ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: