Search

ኢትዮጵያ እና 29 ሀገራት የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትብብር ድርጅት መሰረቱ

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 141

ኢትዮጵያ ከ29 ሀገራት ጋር በመሆን የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትብብር ድርጅትን (WAICO) መሰረተች።

በሻንጋይ እየተካሄደ ባለው የ2026 የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስ (WAIC) ዋዜማ ላይ ሐሙስ ዕለት በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ስምምነቱን በኢትዮጵያ ስም ፈርመዋል።

በጠቅላላው 29 ሀገራት የፈረሙት የዚህ አዲስ ነፃ መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት የማቋቋሚያ ስምምነት ላይ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በሀገራቸው ስም የፈረሙ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ታድመዋል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን በሻንጋይ የሚያደርገው ይህ ድርጅት የተመድ ቻርተር ዓላማዎችን የሚያከብር፣ ለሰፊ ምክክርና ለጋራ ጥቅም በጋራ ለማበርከት ቁርጠኛ የሆነ እንዲሁም ሰውን ማዕከል ያደረገ አካሄድን የሚከተል ነው።

ድርጅቱ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ዓለም አቀፍ ትብብርንና አስተዳደርን ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ ይህም የኤአይ (AI) ልማት ለመላው የሰው ልጅ ጠቃሚ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፍትሃዊ በሆነ አቅጣጫ እንዲጓዝ ለማድረግ ታስቦ የተመሰረተ ነው።

የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድርጅትን (WAICO) የማቋቋም ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይና የቀረበው በሐምሌ ወር 2025 (እ.ኤ.አ.) የኤአይ (AI) ልዩነትን ለማጥበብ እና ከቴክኖሎጂው የሚገኘው ትርፍ ደቡባዊው የዓለም ክፍል (Global South) ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ዘርፈ-ብዙ መድረክ ለመፍጠር ነበር።

ይህ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ሀገራችን ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ለዲጂታል ሽግግር እያሳየች ያለውን እያደገ የመጣ ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና 2030 ስትራቴጂዎችን ጨምሮ የብሔራዊ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋምን በንቃት ሲያስተባብር መቆየቱን እና አሁንም በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: