በውስጧ ድንቅ የሕንፃ ጥበብንና ረቂቅ ሥልጣኔን አቅፋ የያዘቸው ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ፣ የጥንት ስልጣኔዋ ማሳያ ከሆኑት ልዩ ቅርሶች መካከል የጀጎል ግንብ አንዱ ነው፡፡
በ48 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና ዙሪያው 3 ሺህ 342 ሜትር የሚረዝመው ጥንታዊው የጀጎል ግንብ፣ የኢትዮጵያን ጥልቅ ሥልጣኔና የሕንፃ ጥበብ ለዓለም የሚያሳይ ሕያው ሙዚየም ነው።
በውስጡ ጠባብ መንገዶችንና ጥንታዊ ቤቶችን አቅፎ የያዘው ይህ ግንብ፣ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ አምስት ዋና ዋና በሮች የያዘና የጥንታዊቷ ሐረር ልዩ መለያ ነው።
የጀጎል ግንብ ባለው ልዩ የታሪክ ይዘት፣ ጥንታዊ የከተማ ፕላንና የማይጠፋ ባህላዊ እሴት ምክንያት፣ እ.አ.አ በ2006 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ይህ ጥንታዊ የቅርስ ስፍራ በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በየጊዜው የሚጎበኝ ልዩ የቱሪዝም መስህብ ሲሆን፤ በዘንድሮው የ“ልውቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ” መርኃ ግብርም ከተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የ2018 የ“ልውቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ” ታላቁ ሩጫ ማጠቃለያ መርሃ-ግብርን አስመልክቶ፣ በታሪካዊው የጀጎል ግንብና አምስቱ በሮች ዙሪያ የእግር ጉዞ እና ጉብኝት ተከናውኗል፡፡
ይህ ልዩ መድረክ ስፖርትን ከባህልና ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር፣ የሐረርን ከተማ እምቅ የታሪክ፣ የባህልና የኪነ-ህንጻ እሴቶች ለዓለም አቀፍና ለአገር ውስጥ ጎብኝዎች ይበልጥ ያስተዋወቀ ክስተትም ሆኗል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲካሄድ የቆየው የ“ልውቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ” የስድስት ከተሞች የሩጫ ውድድር የዓመቱን የመጨረሻ ማጠቃለያ መርሃ-ግብርም በነገው ዕለት በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: