የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የክልሉን በ2018 በጀት ዓመት ዘርፈ ብዙ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አፈጻጸምን እየገመገሙ ይገኛል፡፡
የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ክልል አቀፍ የአስፈጻሚ አካላትን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 10 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ድረስ 10 ነጥብ 462 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች የታየባቸው መሆኑን አቶ ቃሲም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር የልማት ሥራዎችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ማከናወን ተችሏል፡፡
በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከናወኑ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡
በከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎች የከተሞችን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉን ከተሞች በኮሪደር ልማት ውብ እና ምቹ የማድረግ ሥራ መከናወኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በቀጣይ ዓመት የከተማና የገጠር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለኑሮ ምቹ አካባቢን የመፍጠር ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ስኬት የታየባቸውና የሕዝቡን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በከፍተኛ ትጋት ሥራዎች የተከናወኑበት ዓመት መሆኑን ሀሰን ገልጸዋል፡፡
በዓመታዊው የግምገማ መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቀረበው ሪፖርት በጥልቀት ተወያይተው ለቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል፡፡
በነስረዲን ሀሚድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: