የጠፈር ቴክኖሎጂ ዘርፍ በግል ድርጅቶች እጅ እየገባ ባለበት በዚህ ዘመን፣ የሕንዱ ‘ስካይሩት ኤሮስፔስ’ ኩባንያ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን በግል የበለፀገ ‘ቪክራም-1’ የምህዋር ሮኬት በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ በማስወንጨፍ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
“የአጋማንተልእኮ” የተሰኘው ይህ ታሪካዊ ሥራ በሰሪሃሪኮታ በሚገኘው የሳቲሽ ዳዋን የጠፈር ማዕከል የተከናወነ ሲሆን፣ ሮኬቱ ጉዞውን በጀመረ በ15 ደቂቃ ውስጥ የተሸከማቸውን ጭነቶች በ450 ኪሎ ሜትር ምህዋር ውስጥ ማድረስ ችሏል።
ይህ ስኬት ሕንድን በግል ድርጅት አማካኝነት ሮኬት የማስወንጨፍ አቅም ካገኙ የዓለማችን ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
የቴክኖሎጂ አፍቃሪዎችን ቀልብ የሳበው 22 ሜትር ቁመት ያለው ‘ቪክራም-1’ ሮኬት፣ በዘመናዊ የኢንጂነሪንግ ጥበብ የተዋቀረ ነው።
ሮኬቱ ሦስት የጠንካራ ነዳጅ ደረጃዎችን እና በ3D ታትሞ የተሰራ የፈሳሽ ነዳጅ ሞተርን በማጣመር፣ እስከ 350 ኪሎ ግራም የሚደርስ ጭነት ወደ ዝቅተኛው የምድር ምህዋር የማድረስ አቅም አለው።
በአውሮፓውያኑ 2018 የተመሰረተውና የ1 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ይህ ኩባንያ፣ በቅርቡ ወደ መደበኛ የንግድ በረራዎች ለመሸጋገር ዝግጅቱን አጠናቋል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህ ውጤት ለሀገሪቱ የጠፈር ጉዞ አዲስና ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
“ተልዕኮው የወጣቶቻችንን ተሰጥኦ፣ ቁርጠኝነት እና የስራ ፈጣሪነት መንፈስ ያጎላል” በማለትም ወጣቱን ትውልድ አበረታተዋል።
ሕንድ የጠፈር ዘርፉን ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጓ፣ እንደ ስካይሩት ላሉ ኩባንያዎች ትልቅ በር ከፍቷል።
መንግሥት በበኩሉ፣ የግል ኩባንያዎችን አቅም በመጠቀም የሀገሪቱን የዓለም አቀፍ የጠፈር ኢኮኖሚ ድርሻ በአሁኑ ጊዜ ካለው 8 ቢሊዮን ዶላር በ2033 ወደ 44 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ይህም እንደ ስፔስኤክስ ካሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጋር በአነስተኛ ሳተላይት ማስወንጨፊያ ገበያ ውስጥ ሕንድ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን ዕድል ይሰጣታል።
ይህ ስኬት የቴክኖሎጂ አቅምን ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ በፈጠራና በቁርጠኝነት የማይቻል የሚመስለውን እንቅፋት መስበር እንደሚችል የሚያሳይ ተግባር ነው።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: