የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ምናልባትም ወደር ከማይገኝላቸው፣ በከፍተኛ ስኬታማነቱ ከሚጠቀሱና ለህዝብ ታላቅ እፎይታን ካመጡ ደማቅ ሁነቶች ግንባር ቀደሙ ነው። ይህ ታሪካዊ ስምምነት የታላቅ ሀገራዊ አመራር ቆራጥነት፣ የሰከነ ፖለቲካዊ ጥበብና እውነተኛ የሰላም ፈላጊነት በተግባር የተረጋገጠበት ህያው ማረጋገጫ ነው።
ፅንፈኛው ቡድን ስምምነቱን ቀድዶ ቢጥለውም እንኳን ፕሪቶርያ በታሪክ የሚወሳ የሰላም ጥረትና ቆራጥ ውሳኔ መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም።
በጦርነቱ አውድማ ፍጹም ተሸንፎ፣ አቅሙ ተሟጦና እጅ ለመስጠት ተገዶ በጣረ-ሞት ላይ ለነበረ ኃይል፣ ዳግም ነፍስ ዘርቶ የሰላም ዕድል እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ምስኪኑ ህዝብ ከጦርነት መዘዝና ከሞት ድግስ እንዲላቀቅ የተደረገበት ቆራጥ ውሳኔ ነበር። በመሆኑም፣ ፕሪቶሪያ በስኬታማነቱ፣ በሰብዓዊነቱና ባመጣው አንጻራዊ መረጋጋት በኢትዮጵያ የሰላም ታሪክ ውስጥ ሁሌም በቁጥር አንድነት ሊጠቀስና በከፍተኛ ደረጃ ሊወደስ የሚገባው ታላቅ የስምምነት ሰነድ ተብሎ በኩራት ሊገለጽ ይችላል።
መሰረታዊውና አሳዛኙ ጉዳይ ግን የዚህ ስምምነት ግልባጭ በሌላኛው ወገን በአግባቡ አለመተርጎምና መጣስ ነው። ፕሪቶሪያ እንደታሰበው ህዝብን ሙሉ በሙሉ እፎይ ቢያሰኝ፣ ምስኪኑን ዜጋ ከጦርነት አዙሪት በዘላቂነት ቢያላቅቅ፣ እና ማህበረሰቡን ከግድያና ከመከራ ቢያስጥል እጅግ መልካም ነበር።
አሁን በተግባር እየታየ ያለው መራር እውነታ ግን፣ ይህን ታላቅ የሰላም ስምምነት ላለፉት ዓመታት “እንደ መነገጃ”፣ እንደ ፖለቲካ ታፔላና እንደ ማስፈራሪያ ሲጠቀም መክረሙ ነው። የከሰረው ቡድን ፕሪቶሪያን እንደ መጫወቻ ካርድ በመጠቀም፣ መንግሥትን ለመክሰስ፣ የራሱን ስውርና ጥገኛ ፍላጎት ለማስፈጸም፣ ህዝብን በውጥረት አንቆ ለማቆየትና የሀሰት መረጃዎችን ለመንዛት ሌት ተቀን ሲጠቀምበት ከርሟል።
ይህ ሕገ-ወጥ ቡድን የፕሪቶሪያ ስምምነት ዳግም ትንፋሽ እንዲተነፍስና ከሞት እንዲተርፍ ማድረጉን ተገንዝቦ፣ ለሰላሙ ውለታ ዕውቅና መስጠት ሲገባው፤ ጭራሽ ህዝብን ዳግም መከራ ውስጥ ለመክተት፣ እንደ አዲስ የፖለቲካ ቁማር ካርድ እንዳገኘ ሁሉ በስምምነቱ ጥላ ስር ተደብቆ ያረጀ የፖለቲካ ቁማሩን ሲሰራ ከረመ።
ከስምምነቱ መንፈስ ባፈነገጠ መልኩ፣ በውስጥ ሽኩቻና ሕገ-ወጥ የፈንቅለ-መንግሥት እርምጃዎች በመዘፈቅ፤ ህጻናትን ዳግም ለጦርነት በመመልመል፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት በመፍጠርና አዲስ የጦር ዝግጅት በማድረግ ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ገደል ከቶታል። በመልሶ ማቋቋምና ትጥቅ መፍታት (DDR) ፕሮግራም መሰረት ትጥቃቸውን ፈትተው (Demobilize) ተደርገው ወደ ሰላማዊ ህይወት ይመለሳሉ የተባሉትን ሠራዊቶች መልሶ በማደራጀትና በመመልመል፣ ህብረተሰቡን ዳግም ወደ ስቃይ፣ ወደ ለየለት ውጥረትና የጦርነት ስጋት ውስጥ ለመክተት ቀን ከሌት ተጠምዶበታል።
ይባስ ብሎ ሌሎች የጥፋት ኃይሎችን ጭምር በመጋበዝ ለዳግም ደም መቃባት በግዳጅና በአፈሳ ዝግጅቱን በአደባባይ ሲያደርግ ከርሟል።
ነገር ግን፣ ከዚህ በኋላ ፕሪቶሪያን በፕሪቶሪያ ስም ማጭበርበር ከቶውንም አይቻልም! ፕሪቶሪያን ማን በተግባር እንዳፈረሰው ዓለም በሚገባ ያውቃል፤ የኢትዮጵያም ህዝብ ሂደቱን አጥርቶ ያውቀዋል። በመንግሥት በኩል የተደረገውን አስደናቂ ትዕግስትና የሰላም ጥረትም ሁሉም ተረድቶታል።
ይህ ኃይል ሕገ-ወጥነቱ ከልክ ያለፈ፣ በህዝብ ላይ በጭካኔ የሚረማመድ፣ እና እያንዳንዱን አጋጣሚ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ውስጥ ጭምር የራሱን ጥገኛ ፍላጎት ለማሳካት የሚጠቀምበት አረመኔያዊ ስብስብ መሆኑ ተጋልጧል። ይህ ቡድን ለትግራይ ህዝብም ፈጽሞ የማይጠቅም፣ ለኢትዮጵያ ህዝብም ለዘመናት ነቀርሳ ሆኖ የቆየ፣ ህዝብን በህዝብ የሚያባላና አሁንም ቢሆን የግጭትን ደም የሚያነፈንፍ አጥፊ ቡድን ነው።
ስለሆነም፣ ይህ ህዝብን እንደ ፖለቲካ መሸሸጊያ የሚጠቀም እኩይ ቡድን በተለይ ህዝቡ "በቃ!" ሊለው ይገባዋል። አሁን ህዝብ እውነቱን ከተረዳ ቆይቷል። ነቅቷል! እውነቱን በሚገባ አውቋል! የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ማህበረሰብ የዚህን ቡድን ፀረ-ሰላም ሴራና የጥፋት ጥማት ጠንቅቆ ተረድቶታል። አንድ ጊዜ ፊቱን የመታው የጦርነት ድንጋይ፣ ደጋግሞ እንዲመታው ፈጽሞ አይፈቅድም።
ይህ ቡድን በዋናነት እኩይ ቁማሩን እየተጫወተ ያለው ለዘመናት በዚሁ ቡድን ዋጋ ሲከፍል በቆየው ህዝብ ሕይወት ላይ ነው። በመሆኑም፣ ወጣት፣ እናቶች፣ አባቶችና ምሁራን ይህንን ኃይል "በቃ!" የሚሉበት ሰዓት አሁን ነው። "በቃ! በትውልድ ላይ አትቁምር፤ ከህዝባችን ጋር በጋራ ተናበን ተሳስበን በወንድማማችነት ስሜት ልናድግ ይገባል!" በማለት ጠንካራ ድምጹን እያሰማ ነው። እኛን እንደ ፖለቲካ ምሽግና መነገጃ ልትጠቀምብን አይገባም ብሎ ጽኑ አቋሙን እያሳየ ነው!
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: