Search

በጅግጅጋ ሆስፒታል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጣብቀው የተወለዱ ህፃናት ላይ የተሳካ የቀዶ ሕክምና ተከናወነ

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 82

በሕክምና ሳይንስ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ከሚባሉ የቀዶ ሕክምና ፈተናዎች መካከል አንዱ የሆነው ተጣብቀው የተወለዱ ህፃናትን የመለየት ሂደት፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ሪፈራል ሆስፒታል በድል ተጠናቀቀ።

በሆስፒታሉ የህፃናት ቀዶ ሕክምና ሀኪም ዶ/ር ሰለሞን ውበቱ እንደገለጹት፣ ይህ ታሪካዊ ክስተት በዘርፉ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው።

የተከሰተው የሕክምና ሁኔታ በሳይንሱ “ሄትሮፓገስ መንትያ” ተብሎ የሚጠራ ነው። ይህ ሁኔታ የሚፈጠረው አንድ አይነት መንትዮች በእርግዝና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ሲፈጠሩ ሲሆን፣ አንደኛው ህፃን ከእናቱ በሚያገኘው የተሟላ የደም ዝውውር ተፈጥሯዊ እድገቱን ይዞ ሲያድግ፣ ሌላኛው ህፃን ግን ከእናቱ ጋር ያለው ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት ጤነኛው ህፃን ላይ ተጣብቆ እንዲፈጠር ይገደዳል።

በምርመራ እንደታየው፣ ህፃናቱ በተፈጥሮ የተጣበቁ ሲሆን በአንደኛው ህፃን የግራ ሆድ አካባቢ ተጨማሪ የሰውነት አካላት ተገኝተዋል።

ዶ/ር ሰለሞን እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን ሁለቱም ህፃናት የሚጋሯቸው ዋና የሰውነት ክፍሎች ባይኖሩም፣ ጥገኛውን ክፍል በቀዶ ሕክምና መለየት ለጤነኛው ህፃን ህይወት ወሳኝ ነበር።

በሆስፒታሉ የሕክምና ቡድን የተካሄደው የሁለት ሰዓታት ፈታኝ ቀዶ ህክምና፣ በጤንነት ላይ የነበረውን ህፃን ህይወት ሙሉ በሙሉ ለመታደግ አስችሏል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ሚሊዮን ወሊዶች በአንደኛው ላይ ብቻ የሚያጋጥመው ይህ የሕክምና ሁኔታ፣ በዘመናዊው የሕክምና ጥበብ ታግዞ በሆስፒታሉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በስኬት ተከናውኗል።

ከሕክምና ሳይንስ እድገት ጋር ተያይዞ በመሰል ሁኔታ ውስጥ የሚወለዱ ህፃናትን የመታደግ ዕድል አሁን ላይ ወደ 90 በመቶ ከፍ ማለቱ ትልቅ ተስፋን የፈጠረ ነው።

ይህ በጅግጅጋ ሼክ ሀሰን የበሬ ሪፈራል ሆስፒታል የታየው ድንቅ ስኬት፣ የሀገራችን የሕክምና አቅም ምን ያህል እየገዘፈ እና ተስፋ ሰጪ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ የጋራ ኩራት ሆኗል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: