Search

ፊሽካ እና በትግራይ ከአፈሳ ለማምለጥ የሚደረግ ትንቅንቅ

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 71

በትግራይ ከተሞች፣ ሰፈሮች እና ጠባብ መንደሮች ውስጥ ዛሬ የፊሽካ ድምጽ የውድድር ሜዳ መምሪያ ወይንም የስፖርት ዳኛ መቆጣጠሪያ መሆኑ ቀርቷል።

ዛሬ ላይ ይህች አነስተኛ ፊሽካ የኅልውና፣ የነጻነት እና ከሞት አፋፍ የማምለጫ የነፍስ አድን ደወል ሆናለች። በመቐለ እና በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች፣ ይህን የከሰረና ያረጀ የጥፋት ቡድን አፈሳ ለመሸሽ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በየመንደሩ ጥጋጥግ፣ በየማዕዘኑ እና በየጨለማው ተደብቀው የቆሙ ወጣቶች በሚያሰሙት ቅጽበታዊ የፊሽካ ድምጽ፣ ሌላው ወንድማቸው ከአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ራሱን እንዲያድን፣ አቅጣጫውን እንዲቀይር እና እንዲሸሽ መረጃ ይለዋወጣሉ። ይህ ድምጽ ተራ እምቢተኝነት አይደለም፤ በገዛ ቀያቸው በነጻነት የመኖር ኅልውና ትንቅንቅ እና የነቃ ትውልድ የህይወት ጥሪ ነው።

ወጣቱ ይህንን የፊሽካ መረጃ ልውውጥና የመሸሸግ ስልት የዘየደው ያለ በቂ ምክንያት አይደለም። ላለፉት ዘመናት የትግራይን ሕዝብ ከልክ በላይ እጅግ ከባድ ዋጋ ያስከፈሉ፣ ወጣቱን እንደ ቅጠል ያረገፉ፣ ትርጉም አልባ እና ምክንያት የለሽ ጦርነቶች ያስከተሉትን ጥልቅ የህይወት፣ የሥነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ኪሳራ ይህ ትውልድ በአግባቡ ተረድቶታል።

እናቶች በከንቱ ያለቁ ልጆቻቸውን እያሰቡ የሚያነቡት እንባ ገና አልደረቀም። እኩዩና የከሰረው ቡድን ግን ዛሬም ያ ክፉ አመሉ ሳይለቀው ሕዝቡን የፖለቲካ መሸሸጊያ እና የሴራ ማድሪያ በማድረግ ወጣቱን ለጦርነት እሳት ዳግም ለመማገድ አረመኔያዊ አፈሳውንና አፈናውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ወጣቶቹ ግን የዚህ ጨካኝ ሥርዓት ግፍ ሰለባ ላለመሆን፣ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን አጠናክረው በተደራጀ መንገድ ራሳቸውን ከሞት እያዳኑ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን የዚህ የከሰረ ቡድን አፈና እና ጭካኔ ጠንክሮ፣ ዛሬም በርካታ ወጣቶች በግድ እየታፈሱና የካምፕ እስረኛ እየሆኑ መሆናቸውን መረጃዎች ቢያሳዩም፤ የትግራይ ወጣት ግን ታላቅ የማኅበራዊ ንቃት ንቅናቄ ጀምሯል።

አሁን ጊዜው በትክክል የተለየ ነው፤ ይህ የፊሽካ ድምጽ የለውጥ ፊሽካ ነው፤ የነጻነት ደወል ነው። በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ፣ ህይወቱን እያስከፈለ፣ ልጆቹን በየጦር ግንባሩ እያስበላና ትውልድን እያመከነ ያለውን ይህን ጨካኝ እና አረመኔ ቡድን አውርዶ ለመጣል የተጀመረ የቆራጥነት እምቢተኝነት ነው። ትውልዱ ዳግም የጥፋት ኃይሎች የቁማር መጫወቻ እና የጦርነት ጭዳ ላለመሆን የወሰነበት እንዲሁም እውነቱን በድፍረት የተጋፈጠበት የታሪክ አደባባይ ላይ ቆሟል። የትግራይ ሕዝብ አሁን "በቃ!" ብሏል።

ይህ የህይወትና የሞት ትንቅንቅ በወጣቶች ፊሽካ ብቻ ተወስኖ የሚቆም አይደለም፤ ሊቆምም አይገባውም። መላው የትግራይ ኅብረተሰብ እናት፣ አባት፣ ወጣት፣ ሴቶች፣ ምሁራንና ነዋሪዎች በአንድነትና በጽኑ አቋም ተባብረው ይህንን ፀረ-ሕዝብ ቡድን እስከወዲያኛው ሊያስቆሙት ይገባል።

የዚህ ዘመን የነቃ ወጣት ታሪካዊ ተልዕኮ፣ የጥፋት ኃይሎችን አሽቀንጥሮ በመጣል ከእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ማደግን፣ መሥራትንና መለወጥን እውን ማድረግ ነው። አዲሱ የትግራይ ወጣት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በወንድማማችነት ስሜት ተናቦ፣ በጋራ የልማት ጎዳና ላይ ለመራመድ ቆርጦ ተነስቷል።

ይህ ትውልድ የራሱን ዘመን በጥበብና በትጋት የሚያቀና እንጂ፣ የከሰሩ ፖለቲከኞች ጭዳ የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል። የጥፋት ኃይሎች የጦርነት ነጋሪት ድምጽ፣ በወጣቶች የሰላም እና የህይወት ፊሽካ ተሸንፎ፣ የትግራይ ሕዝብ በሀገሩ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በአንድነት ብሩህ ዘመኑን የሚገነባበት የብርሃን ጊዜ እውን የሚሆንበት ታሪካዊ ምዕራፍ አሁን ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: