Search

የባሕር በር ፍላጎት፤ ለትውልድ ምንዳ እንጂ ዕዳ ላለማውረስ የተጀመረ ጉዞ

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 64

የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ነፃነትና የፖለቲካ ልዕልና በጥብቅ ከተፈጥሮ በረከቶችና ከጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና የሀገርን ክብር ለመመለስ የጀመረችው የባሕር በር ስትራቴጂ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አቀማመጧ እና በረጅም ታሪኳ የባሕር በር ባለቤት ሆና፣ ሀገረ መንግሥቷም በየጊዜው እየሰፋ በመጣ የመሬትና ተፈጥሯዊ የባሕር ግዛት ባለቤት በመሆን፣ ከተለያዩ ሥልጣኔዎችና መንግሥታት ጋር ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመሠረተች ሀገር ነበረች።

ሆኖም ግን የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴና በየዘመናቱ በነበሩ የውስጥና የውጭ የሴራ ኃይሎች ምክንያት፣ ላለፉት ዓመታት የባሕር በር አልባና የሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጥገኛ እንድትሆን ተደርጋ ቆይታለች።

ይህም ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን ሀገር ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራና ለደህንነት ስጋት የዳረገ ሲሆን፤ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይና ለሎጂስቲክስ አገልግሎት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንድትከፍል በማስገደድ የንግድ ተወዳዳሪነቷንና የኢኮኖሚ ዕድገቷን የያዘ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

በሕዝብ ገፊነትና በአመራር ሳቢነት እውን የሆነው ሀገራዊ ለውጥ ይህንን የዘመናት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ቆራጥ አቋም ይዟል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የመደመር መንግሥት፣ የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት እንደማይቻልና እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የኖረበትን ሥነ-ልቦናዊ ስብራት የቀየረ ስትራቴጂ ቀርጿል።

ስትራቴጂው በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመሥረት የተጀመረ ሲሆን፤ ሀገራችንን በጥገኝነት ቀንበር ስር ጠፍረው ለማቆየትና በረብሻ ለማትረፍ የፈለጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን እቅድ አክሽፏል።

ይህ ስትራቴጂ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ክብርና የማንነት መገለጫ ጭምር ነው። የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል መልሶ በማደራጀትና ጠንካራ የባሕር ላይ መከላከያ በመገንባት፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና አስተማማኝ የፀጥታና የደህንነት አጋር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ያላትን መሪነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል መንገድ ከፍቷል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ፍትሐዊና በዓለም አቀፉ የሉላዊነት መርህ ማለትም ሀብትን በጋራና በፍትሐዊነት የመጠቀም እሴት ላይ የተመሠረተ ነዉ።

"ለትውልድ ምንዳ እንጂ ዕዳ አናወርስም" በሚለው ሀገራዊ መርህ መሠረት፣ ይህ የትውልድ የዘመናት ቁጭት የፈታ ታሪካዊ እርምጃ እስከ መጨረሻው ግቡ እንዲደርስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነትና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነዉ።

መላው ሕዝብ አጀንዳውን በባለቤትነት አጥብቆ በመያዝ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ዓለም ለሁሉም ፍትሐዊ እንድትሆን የራሷን ደማቅ የታሪክ ዐሻራ እንድታስቀምጥና ትውልዱም በታሪክ የባሕር በር በማስገኘት ረገድ በጋራ መትጋት ይገባል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: