የፖለቲካ ሥልጣንን ከሕዝብ ህልውና፣ ሰላም እና ደኅንነት በላይ አስበልጦ የሚመለከተው ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ የትግራይን ህዝብ ማለቂያ በሌለው የጦርነት፣ የስደት እና የስቃይ አዙሪት ውስጥ ከትቶት ይገኛል።
ይህ ቡድን "ከእኔ በላይ የሚያውቅ የለም" በሚል የእብሪት እና አምባገነንነት አስተሳሰብ ሲመራ የቆየ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑ ቀርቶ አደገኛ የሽብር ቡድን ወደመሆን ተሸጋግሯል።
ከዘመን ጋር መራመድ ሲያቅተው የሰላም አማራጭን በተደጋጋሚ በመግፋት ህልውናውን በጦርነት እና በደም ብቻ ለማቆየት መወሰኑ የትግራይ ሕዝብ የዘመናት የመከራ እና የጉስቁልና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ውድመት በተመለከተ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ "ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ችግሮችን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የሚሞክር ግትር አቋም ያለው የወንጀለኞች ስብስብ ነው" በማለት የችግሩን ስር መሰረት እና የቡድኑን ፀረ-ሰላም ባህሪ በግልፅ አስቀምጠውታል።
አሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚታየው እውነታ እጅግ ዘግናኝ እና ልብ የሚሰብር ነው። ቡድኑ የራሱን ህልውና ለማስቀጠል ሲል ብቻ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በማስፋፋት፣ ወጣቶችንና ህጻናትን እያፈሰ ለጦርነት ከመማገድ ባለፈ ለሻዕቢያና ለሱዳን ኃይሎች በመሸጥ የገቢ ምንጭ እያደረጋቸው ይገኛል።
ከዚህም አልፎ የጥፋት መንገዱን የማይቀበሉ ሰላም ወዳድ ዜጎችን እስከ ሃያ አምስት ዓመታት በሚደርስ እስራት የሚያሳቅቅ አዲስ አዋጅ "ሕገ አራዊት" አውጥቷል።
በተለይም አዋጅ ቁጥር 336/900/2018 የተሰኘ አፋኝ ህግ በማፅደቅ ቀላል ጥፋቶችን ሳይቀር በሞት እና በዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ አስፈሪ ሥርዓት ዘርግቷል።
ይህ የቡድኑ እኩይ ባሕሪ በትግራይ እናቶች፣ ወጣቶች እና አረጋውያን ላይ እያደረሰ ያለው መከራ ከፍተኛ ነው።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት የቡድኑን የአሁን ቁመና እና የፈጠረውን የሽብር ድባብ ሲገልጹ "አሁን ግን ከአምባገነንነትም አልፎ ሽብርተኛ ድርጅት ሆኗል... ሙሉ በሙሉ ትግራይ ውስጥ ያለው ፍርሀት ከዚህ ድርጅት ሽብርተኛ ባህሪው የተነሳ ነዉ" በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አብራርተዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ የእፎይታ አየር አምጥቶ የነበረ ቢሆንም ሰላም ለህልውናው የሚያሰጋው ይህ ህገ-ወጥ ቡድን ስምምነቱን በገሃድ በመጣስ ዳግም ወደ ጦርነት እያኮበኮበ ይገኛል።
ቡድኑ ከውጭ ኃይላት እና ከሌሎች ፅንፈኞች ጋር "ፅምዶ" በተሰኘ የእኩይ ሴራ ጥምረት የትግራይን ሕዝብ ለባሰ ስደት፣ ሞት እና መከራ የሚዳርግ ብሎም ለማጥፋት እየሠራ ይገኛል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ትናንት "አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን" በሚል መሪ ቃል ባካሄዱት ሰልፍ ላይ እንዳረጋገጡት የሕዝቡ ፍላጎት ሰላም እና ልማት እንጂ ዳግም የጥፋት መሳሪያ መሆን አይደለም።
አባቶች እና እናቶች ያለረዳት እየቀሩ፣ ልጆቻቸው በግዳጅ እየተወሰዱባቸው በከባድ ሀዘን እና ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ።
ይህ ህገ-ወጥ የወንጀለኞች ስብስብ በአረጀውና ከዘመኑ ጋር የማይራመድ አስተሳሰቡ ዳግም ሀገርን ደም ለማፋሰስ ከማሰብ ውጭ ምንም አይነት ዓላማ የለዉም።
አቶ ገብሩ አስራት ይህን ቡድን ዳግም ዕድል ሊሰጠው የማይገባ፣ በታሪክም ሆነ በተግባር የተፈተነ እና ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ገልጸዉ "ከዚህ በፊት ተፈትነው ወድቀዋል፤ እነዚህ ተፈትነው የወደቁ ሰዎች እንደገና አዲስ ነገር ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያመጡለት አይችሉም" በማለት እውነታውን እና የቡድኑን ኪሳራ አስረግጠው ተናግረዋል።
የትግራይን ሕዝብ እንደ ታጋች የያዘው ይህ ሕገወጥ ቡድን የሚያደርገውን አፈና፣ እስራት እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በአስቸኳይ ሊያቆም ይገባል ብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት አዙሪት ወጥቶ በሰላም የመኖር፣ ሠርቶ የመለወጥ እና የልማት ተጠቃሚ የመሆን መብቱ ሊረጋገጥለት ግድ ይላል።
ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ የሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ማኅበረሰብ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት የዚህን ተፈትኖ የወደቀ እና የሽብርተኝነት ባሕሪ የተጠናወተው ቡድን እኩይ ሤራ በማጋለጥ፣ ለዘላቂ ሰላም በአንድነት ዘብ ሊቆሙ ይገባል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: