Search

የ2018 ዓ.ም የ"ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ" ታላቁ ሩጫ ማጠቃለያ በስኬት ተጠናቀቀ

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 114

ባለፉት ስድስት ወራት በደብረ ብርሃን፣ በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በበቆጂ እና በአርባ ምንጭ ከተሞች በስኬት ሲካሄድ የቆየው "ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ" የሩጫ ውድድር፤ ዛሬ ማለዳ መነሻ እና መድረሻውን ሐረር በር በማድረግ በደመቀ ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር፣ የሐረርን የስፖርት ቱሪዝም አቅም እና የጀጎል ግንብን ታሪካዊ እና ባሕላዊ እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሯል። 

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት 10 ኪሎ ሜትር የፕሮፌሽናል አትሌቶች ውድድር በወንዶች ሴና ገመቹ 1 በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን፣ ምሕረት አወቀ እና ኢብራሂም መሐመድ 2 እና 3 በመውጣት የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በሴቶች መካከል በተደረገው ሌላኛው የፉክክር መድረክም ራሔል እምቢበል፣ አምራን ሸምሱ እና አዚዛ ሙክታር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን በድል አጠናቅቀዋል።

በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሰጡት አስተያየት፣ ስፖርት ጤናማ አካል እና አዕምሮ ከማጎናጸፉም በላይ ማኅበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ መተዋወቅን፣ መቀራረብን፣ አብሮ መኖርን እና የሕዝቦችን አንድነት እንዲዳብር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ የተከናወነው ይህ መርሐ ግብር ከተማዋን ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው፤ ይህ ውድድር በሕዝቦች መካከል አብሮነትን ለማጎልበት ያስቻለና በስፖርቱ ዘርፍ አዲስ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በስድስት ከተሞች ሲካሄድ የቆየው 2018 . የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ ታላቁ ሩጫም በታሪካዊቷ ሐረር ከተማ በታላቅ ስኬት መጠናቀቁን ገልጸው፤ አካባቢያዊ ባሕልን፣ ፍቅርንና ስፖርትን በአንድነት ያስተሳሰረው ይህ መርሐ ግብር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በቴድሮስ ታደስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: