Search

ከውስጥ ሰላም እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ፦ የሀገራዊ ምክክሩ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 90

ሀገራችን የጀመረችው አካታች ሀገራዊ ምክክር ከሀገር ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተቀባይነት የበለጠ ለማጎልበት የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው።

አንዲት ሀገር ጠንካራ እና ተሰሚነት ያለው የውጭ ፖሊሲ እንዲኖራት፣ ቅድሚያ የውስጥ አንድነቷ እና ሰላሟ አስተማማኝ መሆን አለበት።

በዚህ ረገድ ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ የውስጥ ቅራኔዎችን እና አለመግባባቶችን በሠለጠነ የውይይት ባሕል በመፍታት፣ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋነኛ የቤት ሥራ የነበረውን የውስጥ አለመረጋጋት ያስወግዳል።

ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መቻሉ ዲፕሎማቶቻችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በሙሉ በራስ መተማመን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁ ጉልበት ይሆናቸዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የውጭ መንግሥታት እና የልማት አጋሮች ከማንኛውም ሀገር ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽም ሆነ የባለብዙ ወገን ግንኙነት የሚቀርጹት በዚያች ሀገር ዘላቂ መረጋጋት ላይ በመመሥረት ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮቿን በሰላማዊ እና አካታች መንገድ ለመፍታት የምታደርገው ጥረት፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላትን አመኔታ በእጅጉ ያሳድገዋል።

ይህ ስኬት ከዋና ዋና የዓለም ኃይሎች እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ስትራቴጂያዊ ግንኙነቶችን ከማጠናከሩም ባሻገር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ እና በአጠቃላይ በአፍሪካ አህጉር ኢትዮጵያ ያላት ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የውስጥ ጥንካሬዋ ቀጥተኛ ነጸብራቅ ነው። የሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት፣ ኢትዮጵያ የውስጥ ቀውሶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምዷን በማካፈልለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔለሚለው መርሕ ተግባራዊ ማሳያ እንድትሆን ያደርጋታል።

ይህም ሀገራችን በቀጣናው ሰላም እና ፀጥታን ለማስከበር፣ በታላላቅ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት ለመደራደር እና ቀጣናዊ መሪነቷን ዳግም ለማስመስከር ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ያጎለብተዋል።

ብዙውን ጊዜ የውጭ ኃይሎች በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚጠቀሙበት ዋነኛው ቀዳዳ፣ በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ የፖለቲካ ክፍተቶችን እና ግጭቶችን በመጠቀም ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር መቻሉ፣ ውጫዊ ኃይሎች የውስጥ ልዩነቶችን እንደ ምቹ ክፍተት እንዳይጠቀሙባቸው በሩን ይዘጋል።

ይህ በዜጎች መካከል የሚፈጠር መደጋገፍ እና አንድነት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር እና የውጭ ተጽዕኖዎችን በጽኑ የሚከላከል ጠንካራ ጋሻ ይፈጥራል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: