Search

ኢትዮጵያ በባሕር በር ጉዳይ የሰከነ ውይይትን እና የጋራ ልማትን መርጣለች

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 117

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትገለል የተደረገችበት መንገድ ሕገወጥ እና የዘመናት ሤራ ውጤት በመሆኑ መብቶቿን ለመጠየቅ ሕጋዊ መሰረቶች አሉአት፡፡

ይሁን እንጂ የራሷ የሆነውን የባሕር በር መልሳ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ፍጹም ሰላማዊ ሕጋዊ እና በሰከነ ውይይት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መርጣለች።

ኢትዮጵያ ይህንን የህልውና እና የዘላቂ እድገት ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የወሰነችበት ዋና ምክንያት ጦርነት እና ጠብ በቀጣናው ከጥፋት እና ከኢኮኖሚ ውድመት ባለፈ ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የሚያተርፉት ምንም ነገር እንደሌለ በፅኑ ስለምታምን ነው።

በምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ምሰሶ የመሆን ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ማናቸውንም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቿን በሰለጠነ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር መምራትን ቀዳሚ ምርጫዋ አድርጋዋለች። ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ መርሕም ይኸው ነው፡፡

በምክክር መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ በሚያጠናክር እና የጋራ ብልጽግናን በሚያረጋግጥ መልኩ ውይይቶችን በሰላማዊ መንገድ እያስቀጠለች ትገኛለች።

ይህ በምክንያታዊነት እና በዲፕሎማሲ ጥበብ ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ አቋም የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ የውጭ ኃይሎች በቀጣናው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ማንኛውንም ድብቅ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚያከሽፍ ስልታዊ መንገድ ነው።

በጥላቻ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ውይይትን እና ሕጋዊ ድርድርን ምርጫዋ ያደረገችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን የነገ ክብር እና ዘላቂ መረጋጋት በማይናወጥ መሠረት ላይ ለመገንባት ጉዞዋን አጠናክራለች።

ይህ ጉዞዋም ጉዳዩን በትክክል በተረዱት ወገኖች ዘንድ ቅቡልነት አግኝቶ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ተዋሳኝነቷ እንድትመለስ ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መኖር ለወቅታዊ ቀጣናዊ ውጥረቶች መፍትሔ እንደሚሆን የሚያውቁትም ኢትዮጵያ ወደምታውቀው ባሕሯ እንድትመለስ እየሠሩ ነው፡፡

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: