ኢትዮጵያ ታሪካዊ በሆነ ውሳኔ እ.ኤ.አ 2024 የብሪክስ (BRICS) ስብስብ አባል መሆኗ በሀገራችን የረጅም ጊዜ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክስተት ነው።
ዓለም ከአንድ ዋልታ የኃይል የበላይነት ወደ ባለብዙ ዋልታ የኃይል ሚዛን በሚሸጋገርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ ወደዚህ ቡድን መቀላቀል ከፍተኛ ጂኦፖለቲካዊ ትርጉም አለው።
ብሪክስ የወታደራዊ ኅብረት ወይም ምዕራባውያንን ለመቃወም የተቋቋመ ጠባብ ቡድን ሳይሆን የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም እና በዘላቂ ልማት ላይ የተመሠረተ አዲስ የዓለም አቀፍ ትብብር ሞዴል ነው።
የብሪክስ እውነተኛ ኃይል እና የህልውናው ሚስጥር የሚገለጠዉም በዘላቂ ልማት ላይ ባለው ጽኑ አቋም እና በተግባራዊ ትብብር ነው።
የብሪክስ አባል ሀገራት በቆዳ ስፋት፣ በኢኮኖሚ አቅም፣ እንዲሁም በፖለቲካ ሥርዓታቸው የተለያየ መልክ ቢኖራቸውም በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በማኅበራዊ መረጋጋት እና ሉዓላዊነትን በማስከበር ላይ ጠንካራ የጋራ ራዕይ አላቸው።
በመሆኑም ብሪክስ አዲስ ዓለም አቀፍ አስተዳደርን እውን ለማድረግ በምዕራባውያን ቁጥጥር ሥር ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ አዳዲስ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ አቅርቦቶችን፣ የኢንዱስትሪ ድጋፎችን፣ እንዲሁም የምግብ እና የኃይል ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ዋነኛ ብሔራዊ ጥቅም የሚጀምረው ታዲያ ከፖለቲካዊ ሉዓላዊነት እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከመከላከል ነው።
በታሪኳ የውጭ ወረራን ተከላክላ ነፃነቷን ያቆየች ሀገር ብትሆንም በዘመናዊው ዓለም ግን በተለያየ መልኩ የሚመጣውን ቀጥተኛ ያልሆነ ፖለቲካዊ ጫና ስትጋፈጥ ቆይታለች።
ምዕራባውያን ሀገራት የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እና የፖለቲካ ጫናዎችን እንደ ፖለቲካዊ ማስፈጸሚያ መሣሪያ የሚጠቀሙባቸዉ ሲሆን፣ ብሪክስ በአንፃሩ የአባል ሀገራትን የውስጥ ጉዳይ በማክበር መርሕ ላይ የቆመ ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የቡድኑ አባል መሆኗ ብሔራዊ ደኅንነቷን እና የፖለቲካ ነፃነቷን ሳታስደፍር ዲፕሎማሲያዊ ከለላ የምታገኝበት ጠንካራ መድረክ ይፈጥርላታል።
ከፖለቲካዊ ነፃነት ባሻገር የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ብሔራዊ ፍላጎት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እና የመሠረተ ልማት ፋይናንስ ማግኘት ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መቀላቀሏ ታዲያ አዲሱን የልማት ባንክ (NDB) ጨምሮ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን እንድታገኝ በር ይከፍትላታል።
ይህም ሀገራችን ለጀመረቻቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ለኃይል አቅርቦት፣ ለግብርና ማዘመኛ እና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ማስፋፊያ የሚሆን ፖለቲካዊ ጫና የሌለበት መዋዕለ ንዋይ እንድታገኝ ያስችላታል።
በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማነቆ ሆኖ የቆየ ሥር የሰደደ ችግር ነው። የብሪክስ አባል ሀገራት በአሁኑ ወቅት የንግድ ልውውጦችን በየራሳቸው ብሔራዊ ገንዘቦች ለማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም እንደ ቻይና፣ ህንድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ካሉ የብሪክስ አባላት ካሉት ዋና ዋና የንግድ አጋሮቿ ጋር የምታደርገውን የገቢ እና የወጪ ንግድ በከፊልም ቢሆን በአማራጭ የገንዘብ ሥርዓቶች ማድረግ መቻሏ፣ በዶላር እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ሊያቃልልላት ይችላል። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚዋን ይበልጥ ተወዳዳሪ እና አቅም ያለው ያደርገዋል።
የብሪክስ ስብስብ ከዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህሉን እና ከዓለም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ግዙፍ ገበያ ነው።
እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች እንዲሁም የተመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ወደነዚህ ግዙፍ ገበያዎች ያለ ታሪፍ ዕንቅፋት መላክ መቻል የኤክስፖርት ገቢን ያሳድጋል።
ከዚህም በላይ፣ ከቻይና የኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ልምድ፣ ከህንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አቅም፣ ከብራዚል የግብርና ማቀነባበር እንዲሁም ከሩሲያ የኃይል እና ማዕድን ቴክኖሎጂ ቀጥተኛ የዕውቀት ሽግግር ማግኘት ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ወሳኝ መወጣጫ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷን ለብሔራዊ ጥቅሟ በስኬት ለማዋል ገቢር ነበብ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መከተልሏተገቢ ይሆናል።
ብሪክስን እንደ ፀረ-ምዕራባውያን መድረክ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ቁልፍ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የልማት አጋሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ስትራቴጂ መሆን ያለበት ብሪክስን በመጠቀም የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ማመጣጠን እንጂ ከአንዱ ወገን ተቆርጦ ወደ ሌላኛው ወገን መለጠፍ መሆን የለበትም።
ብሔራዊ ጥቅም ማለት ሁሉንም የዓለም አቀፍ መድረኮች ለሀገር ግንባታ እና ለሕዝብ ተጠቃሚነት ማዋል ማለት ስለሆነ።
የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ በትክክለኛ አጠቃቀም ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂካዊ መሣሪያ ነው።
ሀገራችን ይህንን ዓለም አቀፋዊ ዕድል ወደ መሬት ወርዶ የዜጎቿን ሕይወት ወደሚቀይር ተጨባጭ የልማት አጋርነት ለመቀየር፣ ከምንም በላይ የውስጥ ሰላሟን እና መረጋጋቷን ማረጋገጥ፣ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንዲሁም ብቃት ያለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን መተግበር ይጠበቅባታል።
ኢትዮጵያ የዓለምን አብላጫ ድምፅ በሚያንፀባርቀው አዲሱ ሥርዓት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ሉዓላዊነቷን እና የኢኮኖሚ ነፃነቷን በተግባር ማስከበር ይገባታል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎቹ የዓለም ሀገራት አዲስ የፖለቲካ ሞግዚት ወይም የርዕዮተ ዓለም ጌታ እያፈላለጉ አይደለም፤ ይልቁንም የራሳቸውን የልማት ጎዳና በነፃነት የሚመርጡበት፣ ቴክኖሎጂ እና መዋዕለ ንዋይ የሚያገኙበትን እውነተኛ አጋርነት ነው የሚሹት።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: