Search

ከሕገ ወጥ ንግድ ወጥቶ ወደ ኢኮኖሚ ምሰሶነት የተሸጋገረው የማዕድን ዘርፍ

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 133

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ሲነሣ የነበረው ከኮንትሮባንድ እና ከተደራጀ ሕገ ወጥ አሠራር ጋር ተያይዞ ነበር።

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ላይ የተደረጉ የአሠራር ለውጦች፣ ማዕድን ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር እያሳዩ ነው።

ለዚህም አንዱ ማሳያ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ 200 ሚሊዮን ዶላር ወደ 3.46 ቢሊዮን ዶላር ማደጉ ነው።

ይህ አኃዝ ዘርፉ ከጥቂቶች መጠቀሚያነት ወጥቶ በቴክኖሎጂ ወደሚመራ እና ተጠያቂነት ወዳለበት ሥርዓት መግባቱን ያሳያል።

ቀደም ሲል ማዕድናትን እንዳሉ በጥሬው ወደ ውጭ የመላክ ልማድ ሰፍኖ ነበር። አሁን ግን በሀገር ውስጥ እሴት የሚጨምሩ የወርቅ ማጣሪያዎች እና ሌሎች ፋብሪካዎች መገንባት ጀምረዋል።

የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን እና ሕገ ወጥ አሠራሮችን በመቆጣጠር፣ 2012 . 3.3 ቶን ብቻ የነበረው የወርቅ ምርት 2017 ወደ 38.83 ቶን ከፍ ብሏል።

ይህም ዘርፉ ምን ያህል አቅም እንዳለው እና ትክክለኛ አሠራር ሲዘረጋ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚችል ያረጋገጠ ክስተት ነው።

ለውጡ በውጭ ምንዛሬ ግኝት ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድም ትኩረት ተሰጥቶታል። ለምሳሌ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ አዳዲስ አምራቾች ወደ ገበያ በመቀላቀላቸው፣ 2014 . 6.2 ሚሊዮን ቶን የነበረው የሲሚንቶ አቅርቦት 2017 ወደ 9.1 ሚሊዮን ቶን ደርሷል።

በተጨማሪም ለሲሚንቶ ምርት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል አሁን ላይ በአራት አዳዲስ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ መተካት ተችሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የካሉብ ጋዝ ሀብት ለማዳበሪያ፣ ለትራንስፖርት እና ለኃይል አቅርቦት እንዲውል መሠረተ ልማቶች እየተዘረጉ ይገኛሉ።

ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ የልማቱ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ነው። አሁን ላይ የአካባቢው ማኅበረሰቦች የሮያሊቲ ክፍያ እና ታክስን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል።

ይህም በአካባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የማዕድን ማውጣት ሥራዎቹ የተፈጥሮ ሚዛንን በማይጎዳ መልኩ እንዲካሄዱም የቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

እነዚህ ጅምሮች ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ መሠረት የጣሉ ናቸው። በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ባላቸው እንደ ሊቲየም ባሉ ማዕድናት ላይ ሰፊ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ለማዋል ታቅዷል።

በማዳበሪያ ፋብሪካ የተጀመረውም እንቅስቃሴ በፔትሮ ኬሚካል እና በተያያዥ ፕሮጀክቶች የሚደገፍ መሆኑ ተነግሯል።

በአጠቃላይ የታዩት እነዚህ ለውጦች፣ የማዕድን ዘርፉ ከሕገ ወጥነት ፀድቶ የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ሊደግፍ በሚችልበት ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: