በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የሀገራችንን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የላቀ የጀግንነት አሻራ ካኖሩት የጦር ክፍሎች መካከል የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ይህ ልዩ ኃይል ሀገራችን ከፍተኛ የህልውና ፈተና ውስጥ በገባችባቸው ወሳኝ የውጊያ አውዶች ላይ ተሰልፎ የውጊያውን ሚዛን በፍጥነት በመቀየር "የውጊያ ማርሽ ቀያሪ" የሚል ወርቃማ እና ደማቅ ታሪክ በደሙ ጽፏል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ በ1969 ዓ.ም የዚያድ ባሬ ተስፋፊ ኃይል ሀገራችንን በወረረበት ወቅት፣ በብርጋድየር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የሚመራው የኮማንዶ እና አየር ወለድ ኃይል ከጠላት ጀርባ ሰርጎ በመግባት ስምሪቱን ማክሸፉ እና ታሪካዊቷን የሐረር ከተማ መታደጉ ትውልድ ሲዘክረው የሚኖር የማይረሳ አኩሪ ጀብዱ ነው።
በተመሳሳይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በናቅፋ ተራሮች ለስድስት ወራት ተከብቦ ለነበረው የ15ኛው ሻለቃ ጦር የደረሰበት መንገድ ሌላው የጀግንነት ጥጉ ነው።
አየር ወለዶቻችን ከ2 ሺህ 500 ሜትር በላይ ከፍታ ላይ በፓራሹት በመዝለል፣ መደበኛውን የአቪዬሽን ሳይንስ ሕግጋት በጣሰ የድፍረት ጥግ የጠላትን ከበባ የሰበሩበት እና ጠላት ራሱ "የተስፋዬ በር" ብሎ የሰየመበት ተጋድሎ እስከ ዛሬ በጀግኖቻችን ልብ ውስጥ በጉልህ ይኖራል።
በግንቦት 1980 ዓ.ም በማይ ሚዶ ላይ በተደረገው እጅግ ከባድ ውጊያም ይህ ኃይል ለሀገሩ የከፈለው ወደር የለሽ እና የመጨረሻው መስዋዕትነት የዚሁ ታላቅ የፍቅር ታሪክ አካል ነው።
ምንም እንኳ ይህ ክፍል የሠራዊታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ ለዘመናት ቢያገለግልም ለረጅም ጊዜ ዘመኑን የዋጀ ግልጽ ተቋማዊ አደረጃጀት ሳይሠራለት መቆየቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በተካሄደው ጥልቅ ሁለንተናዊ እና ስኬታማ የሪፎርም ሥራ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸጋግሯል።
ይህ ታሪካዊ ሪፎርም ዕዙን ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የብሔር እና የሃይማኖት ወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ በማላቀቅ ሀገራዊ ፍቅርን እና ሙያዊ ብቃትን ብቻ ማዕከል ያደረገ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የኩራት ምንጭ እንዲሆን አስችሎታል።
የዕዙ አባላት በዘመናዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት ከፍተኛ፣ ዘመናዊ እና እጅግ ፈታኝ የሥልጠና ሂደቶችን በማለፍ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ከነባሩ አሠራር በመውጣት ከአየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች እና ሄሊኮፕተሮች ጋር በመቀናጀት፣ ከዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂ ጋር ተናብቦ በመሥራት፣ እንዲሁም ዳግም ከተዋቀረው የባሕር ኃይል ጋር በመሆን ፈጣን፣ መብረቃዊ እና የተዋጣለት የጥምር ውጊያ ስምሪቶችን ለማካሄድ የሚያስችል ሙሉ አቅም ገንብቷል።
ይህ የተቋማዊ ሪፎርሙ ፍሬ ሠራዊቱ በማንኛውም ግንባር እና ጊዜ የሚነሳን የደኅንነት ስጋት በቅጽበት ለመቀልበስ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ዘመን ተሻጋሪ ብቃት እንዲላበስ አድርጎታል።
ዛሬ ላይ ቆመን ስናየው አየር ወለዶቻችን የትናንቱን አኩሪ ታሪክ በዛሬው ዘመናዊ ልቀት አስጊጠው የሀገራችንን ሰማይ እና ምድር በንቃት የሚጠብቁ የሰላማችን ዋስትናዎች ናቸው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: