Search

ሟርት እና ሙሾን ያሸነፈው ሀገራዊ ምክክር

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 196

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሒደት የውልደት፣ የዕድገት እና የተግባር ጉዞ ከተጀመረ እነሆ አራት ታሪካዊ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ሀገራዊ ኹነት፣ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እንደሚስተዋለው የጥቂት ልሂቃን የፖለቲካ ድርድር ብቻ አይደለም።

ይልቁንም፣ ሰፊውን ማኅበረሰብ ከመሠረቱ ያሳተፈ፣ ጥልቅ እና ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሀገራዊ የውይይት ዐውድማ ነው። የምክክር ሒደቱ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመራ፣ የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ ያዳመጠ እና ጽኑ ማኅበራዊ መሠረት ላይ የቆመ ነው።

የአንድ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ቅቡልነት በሚዛን የሚለካው በሦስት መሠረታዊ ምሰሶዎች ላይ ቆሞ ሲገኝ ነው። እነርሱም፦ የሒደቱ ገለልተኝነት፣ የአካታችነት ስፋት እና የሕጋዊ መሠረቱ ጥንካሬ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በእነዚህ ሦስቱም መመዘኛዎች ወደር የለሽ ስኬት ያስመዘገበ ነው። በመጀመሪያ፣ በአዋጅ በግልጽ እንደተደነገገው ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ እና ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀትን ተከትሏል፤ መንግሥትም ከማገዝ እና የማመቻቸት ሚና ውጪ በምክክሩ ጣልቃ እንዳይገባ ሕጋዊ ማዕቀፍ ተበጅቶለታል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ከፖለቲካዊ አካታችነት አንጻር፣ ሒደቱ በሩን ለሁሉም ወለል አድርጎ የከፈተ ነው። የሃይማኖት አባቶችን፣ አርቲስቶችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ተፎካካሪ ኃይሎችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አዛውንቶችን እና ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በሺሕዎች በሚቆጠሩ ቀበሌዎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ያሳተፈ ታላቅ የፖለቲካ ውይይት መድረክ መፍጠር ችሏል።

ይህ አካታችነት ማንም "አልተወከልኩም" እንዳይል የፍትሐዊነት ማዕዘን ድንጋይ ሆኗል።

ሦስተኛው ምሰሶ፣ ሒደቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለሕዝብ ግልጽ የነበረ እና የሕዝብን አመኔታ ያገኘ መሆኑ ነው። ከማንኛውም ቡድን ወይም የፖለቲካ ፍላጎት ነፃ ሆኖ መደራጀቱ የትኛውንም የዓለም አቀፍ የምክክር መመዘኛ የሚያሟላ፣ አልፎ ተርፎም የሚበልጥ እንጂ የማያንስ ዐቢይ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ወደር የለሽ አካታችነት እና ገለልተኛ ሒደት፣ ለዘመናት በተጣመመ እና በተበላሸ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ ላደጉ ጥቂት ኃይሎች ሊዋጥላቸው አልቻለም።

የሀገራችን የፖለቲካ ባህል "እኔ አውቅልሃለሁ" "እኔ የምለው ብቻ ይፈጸም" በሚል የዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት የተቃኘ በመሆኑ፣ የሐሳብ ልዩነትን በሠለጠነ ጠረጴዛ "ሰጥቶ መቀበል" እንደ ትልቅ ሽንፈት ይቆጠራል።

በመሆኑም ገና ኮሚሽኑ ከማኅፀን ሲፈጠር ጀምሮ ማማረርና መጮህ የጀመሩ፣ "ይህ ምክክር አይሳካም" በሚል የሟርት ዜማ ያላዘኑ አልቃሾች ዛሬም አልጠፉም።

እውነታው ፍንትው ብሎ እንደሚታየው፣ በእነዚህ ኃይሎች ፊት የምክክሩ ሒደት እንደ ሰማይ ቢጠራ፣ እንደ ምንጭ ውኃ ኩልል ቢልም ፈጽሞ ሊደሰቱ አይችሉም። ምክክሩ በሩን ወለል አድርጎ የጠራቸው ቢሆንም፣ የሀገራዊ መግባባት መድረኩ እነርሱ የሚፈልጉትን ጠባብ የቡድን ፍላጎት በጉልበት የሚያስፈጽሙበት ስላልሆነ፣ ውድቀትን ይመኙለታል።

በሕዝብ የጋራ ድምፅ እና በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ የሐሳብ ሙግት ማሸነፍ እንደማይችሉ ስላወቁ፣ መፍትሔያቸው ምክክሩን ማናናቅ ብቻ ሆኗል። ቀድሞ ለናቀ ማርም ሬት ነውና የእነዚህን ሰዎች የፖለቲካ ጥማት ለማርካት የተለየ ተዓምር ቢፈጠር እንኳ ፍላጎታቸውን ማሟላት አይቻልም።

ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነዚህ ሟርተኞች የለቅሶ ዜማ እጅግ የላቀ ሥልጡን፣ ለሰላሙም ቀናኢ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። ሕዝቡ ሒደቱን በንቃት ተከታትሎ፣ ከኮሚሽነሮች ምርጫ አንሥቶ፣ በአጀንዳ ማሰባሰብ፣ በመገምገም እና በማጽደቅ ታሪካዊ አሻራውን አሳርፏል።

እነሆ ዛሬም ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ እውነተኛ የሕዝብ ተወካዮች በአንድ ታላቅ አዳራሽ ተሰብስበው የነገዋን ሀገር ዕጣ ፈንታ እየመከሩበት ይገኛሉ።

ለኢትዮጵያውያን ከውጤቱ በላይ ዋነኛው ቁም ነገር፣ በዐበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን ማቀራረባቸው እና በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መሰባሰባቸው ነው።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጥፋት ነጋሪቶችን ጩኸት እና የነቃፊዎችን ክፉ ምኞት ወደ ጎን በመተው ታላቅ ሀገራዊ ድል ተቀዳጅቷል። ሕዝቡ ለምክክሩ ስኬት እያደረገ ላለው ጥረት የላቀ አድናቆት ሊሰጠው ይገባል።

አዎ! የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸንፏል! ሀገራዊ ምክክሩም የተቃጣበትን ማናናቅ፣ ሟርት እና ለቅሶ በጣጥሶ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በጠንካራ የዴሞክራሲ እና የመግባባት መሠረት ላይ ለማኖር በድል አድራጊነት ይገሰግሳል።

ኢትዮጵያም ይህንን ወርቃማ የሐሳብ ልዕልና አውድማ በመጠቀም፣ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታዋን በማይናወጥ መሠረት ላይ አጽንታ ትቀጥላለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: