Search

በትግራይ ሕዝብ መነገድ ጊዜው አብቅቷል

እሑድ ሐምሌ 12, 2018 263

በታሪክ ማኅደር ውስጥ፣ የሕዝብን ስሜት እና ጥልቅ መከራ እንደ ርካሽ የፖለቲካ ሸቀጥ በመቁጠር ለዘመናት የነገደው የህወሓት ቡድን የጨለማ ጉዞ፣ እነሆ ዛሬ ወደማይቀለበሰው የፍፃሜ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ይህ ኃይል ለዓመታት "እኔ ብቻ ነኝ የምጠቅምህ፣ ከእኔ ውጪ ማንም አይቆረቆርልህም፤ ጎረቤቶችህ፣ ሌላው የሀገርህ ሕዝብ እና ዓለም ሁሉ ለአንተ ቀንደኛ ጠላትህ ነው" በሚል አሰልቺ፣ ጊዜ ያለፈበት እና መርዛማ ነጣይ ትርክት የትግራይን ሕዝብ ለማደንዘዝ ሲሞክር ቆይቷል።

"ስለ አንተ ብቻ ስል ተጎዳሁ፣ መከራህን ሁሉ በጫንቃዬ ተሸከምኩ፣ እኔ ከሌለሁ ታልቃለህ፤ ምድር ከእኔ ውጪ አትሆንህም" የሚለው የማስመሰል እና የሐሰት ካባ፣ ከጀርባው እጅግ ጥልቅ የሆነ ራስ ወዳድነትን፣ የጥቅም ስግብግብነትን እና የሥልጣን ጥማት አባዜን የደበቀ ነበር።

ይህ ቡድን ራሱን እንደ ብቸኛ የትግራይ ሕዝብ አዳኝ፣ ማንነት ሰጪ፣ አሳቢ እና ተቆርቋሪ አድርጎ ሲስል፣ በተግባር ግን የሕዝቡን የነፃነት አየር የሚገታ፣ ትንፋሽ የሚያሳጣ ግዙፍ አምባገነናዊ ግንብ ሲገነባ እንደነበር ያለፉት ዘመናት በግልጽ መስክረዋል።

ይህን የተንሸዋረረ የሐሰት ትርክቱን ለማጽናት እና ዕድሜውን ለማራዘም የተጠቀመበት መንገድም የፍቅር፣ የውይይት እና የምክንያት ሳይሆን፤ የከፋ የጭካኔ እና የጉልበት አፈና ነበር።

የተለየ ሐሳብ ያነገቡ፣ ለትግራይ ሕዝብ የተሻለ የሰላም፣ የልማት እና የዕድገት አማራጭ ለማቅረብ የሞከሩ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወገኖችን በጠላትነት ፈርጆ አሳድዷል፤ በየእስር ቤቱ አጉሯል፤ ከዚህም አልፎ ሕይወታቸውንም በግፍ ቀጥፏል።

ፍላጎቱ የትግራይ ሕዝብ የሐሳብ ብዝኃነትን በነፃነት እንዳያስተናግድ፣ ዓለም የደረሰበትን የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የመቻቻል እሴት እንዳይቋደስ አግቶ በመያዝ እስረኛ አድርጎ ማኖር ነው። ሕዝቡን የፍላጎቱ ማስፈጸሚያ እና መደራደሪያ ማስያዣ አድርጎት፤ ምኅዳሩን ደግሞ በደም፣ በዕንባ እና በብረት አጥሮት ቆይቷል።

ዛሬ ላይ ቆመን፣ ከስሜት ርቀን ወደ ኋላ ስንመለከት፣ ይህ እኩይ ኃይል ባለፉት ዓመታት ለትግራይ ሕዝብ በተግባር ምን ፈየደለት? ምንስ ተዓምር አበረከተለት? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።

እውነታው እጅግ መሪር፣ አንጀት አቁሳይ እና ልብ ሰባሪ ነው። ከልማት ይልቅ ጥልቅ የኑሮ ድቀት፣ ከሰላም ይልቅ የማያባራ የጦርነት አዙሪት አስረክቦታል።

የትግራይ ወጣት ደብተር እና እስክሪብቶ ይዞ የነገ ብሩህ ሕይወቱን ከማለም እና ሀገሩን ከማገልገል ይልቅ፣ ክላሽንኮቭ እና ላውንቸር ተሸክሞ ግብ በሌለው የሞት አውድማ እንዲማገድ፣ ወጣትነቱም በከንቱ እንዲቀጭ ፈርዶበታል።

እናቶች በምጥ የወለዷቸውን ልጆች በከንቱ አጥተው የወላድ መካን እንዲሆኑ፣ አባቶች በስተርጅና ምርኩዛቸውን እንዲነጠቁ አድርጓል። የትግራይ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ወንድም እና እህቶቹ ጋር ተዋዶ፣ ክልሉን አበልጽጎ በሰላም፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ከመኖር ይልቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሥጋት፣ በሰቀቀን እና በፍርኃት ታጥሮ እንዲኖር አድርጎታል።

ከዕዳ፣ ከፍዳ፣ ከከፋ ድህነት እና ከማያባራ የደም አፋሳሽ ግጭት ባለፈ፣ ይህ ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ያመጣው አንድም የረባ በረከት የለም። ሕዝቡም ይህንን አሳዛኝ እውነት እና የቡድኑን እውነተኛ ማንነት በሚገባ ተረድቶታል።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች እና መንደሮች "አሁንም ድጋፍ አለኝ" ለማስመሰል፣ ሕዝብን በግዴታ በማስወጣት የሚያደርገው ፖለቲካዊ መፍጨርጨር፣ የሞት አፋፍ ላይ ያለ ፍጡር የቀቢፀ ተስፋ መንፈራገጥ፣ የታረደ አካል የመጨረሻ ግርግር እንጂ የእውነተኛ ሕዝባዊ አጋርነት መገለጫ አይደለም።

አዎ! በሕዝብ ስም መነገድ ጊዜው ፈጽሞ አብቅቶለታል። የህወሓት መራራ እና የጨለማ ዘመን አቆልቁሏል። ቡድኑ ከትውልዱ የሰላም ጥማት ተለይቷል፣ ከዘመኑ የሥልጣኔ ጉዞ ወደ ኋላ ቀርቷል። በሕዝብ ስም እየነገዱ ለግል ማትረፍ፣ በሕዝብ ደም እየተራመዱ የሥልጣን ኮርቻ ላይ መፈናጠጥ ከእንግዲህ ቦታ የለውም። የዚህ ክፉ ቡድን የውሸት ትርክት በሕዝቡ ንቃተ ሕሊና ውስጥ ለዘላለም ተፈትቶ ወድቋል። አሁን መላው የትግራይ ሕዝብ ያንዣበበበትን የጦርነት ዳመና ገፎ፣ ከሌላው ወንድሞቹ ጋር አብሮ የሰላም እና የልማት ተቋዳሽ የሚሆንበት፣ የብሩህ ተስፋ ንጋት ከፊቱ በሰፊው ተመቻችቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: