በአካባቢያችሁ ድንገት እሳት ቢነሳ ፈጥኖ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው መፍትሔ ምንድን ነው? ውሃ ማፍሰስ፣ በልብስ መሸፈን ወይስ የእሳት አደጋ መጥራት? ይህ የድንጋጤ ጥያቄ ያሳሰባቸው ፈረንሳይ እና ስፔን ግን እጅግ አስገራሚና ያልተጠበቀ መፍትሔ ይዘው ብቅ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አውሮፓን ከባድ የሰደድ እሳት አደጋ እያጠቃት ይገኛል። የዚህ አደጋ ሰለባ ከሆኑት ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ጣሊያን በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ይሁንና ፈረንሳይ እና ስፔን ከዚህ አስከፊ አደጋ ራሳቸውን ለመከላከል የተጠቀሙት ጥበብ ብዙዎችን አስገርሟል። በተለምዶ እሳት ሲነሳ መፍትሔው የእሳት አደጋ ተከላካዮች፣ የውኃ መኪኖች ወይም ሄሊኮፕተሮች ቢሆኑም፣ እነዚህ ሀገራት ግን ፍየሎችን፣ በጎችንና አህዮችን በመጠቀም ልዩ ተፈጥሯዊ የእሳት መከላከያ ዘዴን መርጠዋል።
ታዲያ እንስሳቱ እሳትን እንዴት ይከላከላሉ? ነገሩ እንዲህ ነው። እነዚህ የቤት እንስሳት ደረቅ ሳርና ቁጥቋጦዎችን በመመገብ እሳቱን በቀላሉ ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ "ነዳጅ" የሆኑ እፅዋትን ከምድረ ገጽ ያጸዳሉ።
በዚህም ምክንያት እሳት ቢነሳ እንኳ በፍጥነት የሚዛመትበት ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር ያደርጋሉ። በተጨማሪም እንስሳቱ በዱር ውስጥ በሚያደርጉት ግጦሽ የእፅዋት ክምችትን በመቀነስ፣ እሳት በቀላሉ የማይሻገርባቸውን የተፈጥሮ መከላከያ መስመሮች ይፈጥራሉ። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ፣ እረኞች እንስሳቱን በጂፒኤስ (GPS) ቴክኖሎጂ በመከታተል የትኞቹ አካባቢዎች ተጨማሪ ግጦሽ እንደሚያስፈልጋቸው መለየት መቻላቸው ነው።
ይህ ዘዴ ተግባራዊ የተደረገው ሀገራቱ በተደጋጋሚ ለከፍተኛ የዱር እሳት አደጋ ከተጋለጡ በኋላ ነው። በከፍተኛ ሙቀት፣ በደረቅ የአየር ሁኔታ እና በኃይለኛ ንፋስ ምክንያት የሚነሱ ሰደድ እሳት በፍጥነት በመዛመታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ከአደጋ ቀጠናዎች ለመፈናቀል ተገድደዋል።
ለምሳሌ በፈረንሳይ የጂሮንድ ክልል እና የካፕ ፌሬ አካባቢዎች በእሳቱ ክፉኛ በመጎዳታቸው ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ አገሪቱም ከአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ ድጋፍ እስከመጠየቅ ደርሳለች።
በጣሊያንም የሲሲሊ ደሴትና ሌሎች ደቡባዊ ክልሎች ተመሳሳይ ሰለባ ሆነው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲፈናቀሉ በአደጋው ላይ ሲሰራ የነበረ አንድ የእሳት አደጋ ተከላካይም ህይወቱን አጥቷል። በስፔንም በማድሪድ፣ ጉዋዳላሃራ እና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱ የዱር እሳቶች ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ሲያፈናቅሉ፣ በርካታ ቤቶችና ሰፋፊ የደን መሬቶች ወድመዋል።
ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሙቀት ማዕበሎች ይበልጥ እየተባባሱ በመምጣታቸው በደቡብ አውሮፓ የዱር እሳት አደጋዎች በስፋት እየተደጋገሙ ነው።
በዚህ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ፍየሎች፣ በጎችና ላሞች ከእረኞችና ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በመጣመር እሳትን ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚረዱ ድንቅ የተፈጥሮ ተከላካዮች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ይህ አካሄድ የዱር እሳትን ከተነሳ በኋላ ለማጥፋት ከመታገል ይልቅ፣ ገና ከመጀመሪያው እንዳይበረታና እንዳይዛመት የሚያደርግ ብልህ የቀድሞ መከላከል ስልት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በቃልኪዳን ማዕድን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: