በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የውይይት መድረክ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙትን ወላጆቻቸውን ተከተለው በአዲስ አበባ የሚገኙ ህፃናትና ታዳጊዎች፣ ከዚህ ታሪካዊ ምክክር ትልቅ ተስፋ እንዳላቸውና የተሻለች፣ ሰላማዊትና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሚፈልጉ ገለፁ።
ኮሚሽኑ ልጆቻቸውን ይዘው ለሚመጡ ተመካካሪዎች ባዘጋጀው የልጆች ማቆያ ስፍራ እድሜያቸው ከአምስት እስከ 18 ዓመት የሆናቸው ህፃናትና ታዳጊዎች ይገኛሉ።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡት እነዚህ ህፃናት፣ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ባህሪ ያላቸው ቢሆንም በቆይታቸው ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአንድነት፣ በፍቅር እና በተስፋ ተሰባስበዋል።
ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ከዱራሜ ከተማ ከእናቷ ጋር የመጣችው የ11 ዓመቷ ህፃን ያዳ ታምራት፣ ከወለጋ የመጣው ሰኚ ቡልቻ እና ከአርባ ምንጭ የመጣው ያሬድ አፈወርቅ የሀገራዊ ምክክሩ አወንታዊ ውጤት ለነገ ህይወታቸው ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
ህፃናቱ እንደሚያስረዱት፣ ወላጆቻቸው የተሰበሰቡት የአካባቢያቸውንና የሀገራቸውን ችግሮች በውይይት ለመፍታት በመሆኑ፣ ይህ ምክክር በሰዎች መካከል ያለውን መጥፎ ሀሳብና ግጭት አጥፍቶ ሰላምና አንድነትን እንደሚያስፍን ፅኑ እምነት አላቸው።
ወላጆች ስለ ሀገር የወደፊት እድል በሚመክሩበት ወቅት ስለ ልጆቻቸው ደህንነት እንዳይጨነቁና ሙሉ ትኩረታቸውን በውይይቱ ላይ ብቻ እንዲያደርጉ የታሰበው የልጆች ማቆያ ማዕከል፣ ለህፃናቱ ምቹ የሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።
የማዕከሉ አስተባባሪዎች እንደሚገልፁት፣ ህፃናቱ ጠዋት ከወላጆቻቸው ከተረከቡ በኋላ በደረጃው በተዘጋጀ ስፖርታዊ ሜዳ እንዲጫወቱ በማድረግ ሙሉ እንክብካቤ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኙ ታዋቂ የቱሪስት መስህቦችን እንዲጎበኙ በመደረጉ፣ አብረው በሚያሳልፉት ጊዜ የርስ በእርስ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ወጋቸውንና ታሪካቸውን የመለዋወጥ ደስ የሚል አጋጣሚ አግኝተዋል።
የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከቡት እነዚህ ታዳጊዎች ከትልልቆቹ ውይይት የሚጠብቁት ትልቁ ስጦታ ሰላማዊት ሀገርን ሲሆን፣ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት እንደሚቻል ከወላጆቻቸው መማር ይፈልጋሉ።
የህፃናቱ ንፁህ ምኞትና ትልቅ ተስፋ ለሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ተጨማሪ የኃላፊነት ስሜት የሚፈጥር ሲሆን፣ የዛሬዎቹ ታዳጊዎች ነገ የሚያድጉባት ኢትዮጵያም ከዛሬው የምክክር ጠረጴዛ ውጤት ቅርፅ እንደምትይዝ ይታመናል።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: