በ2019 ዓመተ ምህረት የትምህርት ዘመን በግል ትምህርት ቤቶች በሚካሄደው የተማሪዎች ምዝገባ፣ የክፍያ ጭማሪና የግብዓት ጥያቄ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለፉት ዓመታት የግል ትምህርት ቤቶች በወርሃዊ ክፍያ፣ በምዝገባ፣ በዩኒፎርም እንዲሁም በዓይነት በሚጠይቋቸው እንደ ሳሙና እና ሶፍት ባሉ ቁሳቁሶች ምክንያት በወላጆች ዘንድ ሰፊ ቅሬታ ሲነሳ መቆየቱ ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ይህንን ችግር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት የትምህርት ቤት ወርሃዊ ክፍያ ጣሪያ በመወሰን ትምህርት ቤቶች በዘፈቀደ ያልተገደበ ክፍያ እንዳይሰበስቡ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በ2019 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረግ የሚፈቀድላቸው በደንቡ መመሪያ መሰረት ከዚህ ቀደም ጭማሪ ያላደረጉ 166 የግል ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ታጋይቱ አባቡ ለኢቲቪ ገልጸዋል።
አያይዘውም ከእነዚህ ውጪ ያሉ ቀሪ ሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች ምንም አይነት የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል።
ባለፈው ዓመትም መመሪያውን በመጣስ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ወላጆች ላይ የጽዳት መጠበቂያዎችንና ወረቀት በዓይነት የጠየቁ 149 ተቋማት በክትትልና በወላጆች ጥቆማ ተለይተው እርምጃ እንደተወሰደባቸው የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጇ፣ ቀደም ሲል በዓይነት ይጠየቁ የነበሩ ግብዓቶች መመሪያውን የሚጥሱ በመሆናቸው አሰራሩ እንዲቆም መደረጉንም አብራርተዋል።
ወላጆች ለአዲስ ተማሪዎች የፈተና ክፍያን ጨምሮ ሌሎች ያልተፈቀዱ ክፍያዎች ሲጠየቁ ወይም ግብአቶችን በዓይነትና በገንዘብ እንዲያቀርቡ ሲገደዱ በነፃ የስልክ መስመር 9023 ወይም በአካል በመቅረብ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸው፤ ባለስልጣኑ መመሪያውን በሚጥሱ ተቋማት ላይ የሚያደርገውን ጥብቅ ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: