Search

የሀገር ህልውና እና የቀጣናዊ መረጋጋት ምሰሶ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ አቅምና ታሪካዊ ስኬት

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 64

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወርቃማ እሴቱ በሆነው "በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት" በሚለው መሪ መርሁ መሰረት በተሰማራበት ሀገራዊ  አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎች ሁሉ የላቀ ብቃቱን እያስመዘገበ ይገኛል።

ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና የድንበር ደህንነትን ከመጠበቅ ባለፈ የሕዝቦች ሰላምና የወደፊት የብልጽግና ጉዞ አስተማማኝ ዋስትና መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

በመደመር መንግሥት የሪፎርም ሥራዎች ትኩረት ከተሰጣቸውና ከፍተኛ ስኬት ከተመዘገበባቸው ተቋማት መካከል መከላከያ ሠራዊት ዋነኛው ሲሆን በተለይም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ሠራዊቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በጥራት ስልጠና እና በዘመናዊ አሰራር የማደራጀቱ ስራ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ አቅም እንዲኖረው አስችሎታል።

በዚሁ የመዋቅርና የአቅም ግንባታ ሂደት ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚይዘው ስፍራ ከፍተኛ ሲሆን  ዕዙ በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን በላቀ የአካልና የሥነ-ልቦና ዝግጁነት እንዲሁም በዘመናዊ የውጊያ ስልቶች የተገነባ የሰው ኃይል በማፍራቱ ሀገር በገባችበት የፈተና ወቅት ሁሉ ውጤታማና አሸናፊ ምላሽ በመስጠት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታን አትርፏል።

አባላቱ የሚያልፉት የስልጠና ሂደት መደበኛ አካላዊ ብቃትን ብቻ ሳይሆን ውስብስብ የውጊያ ስልቶችን  ፈጣን ውሳኔ አሰጣጥንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በጥልቀት ያካተተ ነው።

በተጨማሪም ዕዙ በላቁ የክትትል ድሮኖች በዘመናዊ የመገናኛ ሥርዓቶችና በሌሎች ቴክኖሎጂያዊ አቅሞች የተደገፈ በመሆኑ በውጊያ ሜዳ የመረጃ የበላይነትንና የውሳኔ ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል።

ሠራዊቱ ዝግጁነቱን በየብስ፣ በተራራ እና በወንዞች ላይ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ባለፈ ወደ ባሕር ኦፕሬሽኖችም በማስፋት በባሕር ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከልና የወንድማማች ሕዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ገንብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ዕዙ ቀደም ሲል በሰጡት ሀሳብ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ የሽብር ስጋቶችን ለመመከት ወንድማማች ሕዝቦችን ለመደገፍና በቀጣናው ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ኤሊት ፎርስ መገንባቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የዕዙ አባላት "የቀይ ቦኔት" ክብር የገባቸው ለሀገር ሰንደቅ ዓላማና ለነፃነት ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ ከብሔር እና ከፖለቲካ ውግንና ነፃ ሆነው ሀገርን የማጽናት አደራ የተቀበሉ የሀገር አለኝታዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ዛሬ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በየብስ፣ በአየር እና በባሕር የሚሰጡ ግዳጆችን በብቃት ለመፈጸም የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ አቅም በመገንባት በማንኛውም ሁኔታ ተልዕኮውን በስኬት ለመወጣት በሙሉ ዝግጁነት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገር በሰላም እንድትቀጥል በልማት ጎዳናዋ እንዳትገታና የውጭ ተጽዕኖዎችን እንድትቋቋም እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነዉ።

ሠራዊቱ በተሰማራበት የትኛውም ዓይነት ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግዳጆች ላይ ተልዕኮውን እንደ አንድ ሙያተኛ (የሰለጠነ/የበቃ) ሠራዊት በብቃት እየተወጣ የሚገኝና በየትኛውም ተግባሩ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ ያለ ሲሆን፣ በተልዕኮ አፈፃፀሙ ከውጭም ሆነ ከውስጥ በርካታ ክብርና አድናቆቶችን በተለያዩ መንገዶች እየተቸረው ያለ ሕዝባዊ የድል ሠራዊት ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: