በጅማ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ከ1 ሺህ 876 በላይ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር ገለጹ።
በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ የተገነቡ ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል መንገድ፣ ድልድይ፣ የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኬላ፣ የገበያ ማዕከል፣ የግብርና ግብዓት መጋዘን እና የወረዳው አስተዳደር ህንፃን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል።
የዞኑ አስተዳዳሪ በወቅቱ እንዳሉት የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በመንግስት እና በህዝብ ተሳትፎ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርገዋል ብለዋል።
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት በ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ከ1 ሺህ 876 በላይ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልከሪም አባራያ በበኩላቸው በወረዳው በበጀት ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸው ከተጀመሩ 33 ፕሮጀክቶች ውስጥ 23ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረጉ አመላክተዋል።
የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተደረገ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሀመድ ዘይን ተማም ናቸው።
አቶ አበዱላሂ አባ ጀበል በበኩላቸው በወረዳው ዶዩ ቃጨማ ቀበሌ የተገነባው የግብዓት ማቆያ እና ማከማቻ ከዚህ ቀደም የግብርና ግብአቶችን ለማግኘት ወደ አጎራባች ወረዳዎች በመጓዝ የሚባክንን ግዜና ገንዘብ እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: